Fana: At a Speed of Life!

ጨፌው የረቂቅ ሕግ አዘገጃጀት ሥርዓትን የሚወስን አዋጅን አጸደቀ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 11፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ጨፌ ኦሮሚያ በሁለተኛ ቀን ውሎው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የረቂቅ ሕግ አዘገጃጀት ሥርዓትን ለመወሰን የወጣ አዋጅን ተወያይቶ አጸደቀ።

አዋጁ የሚረቀቁ ሕጎች ጥራት፣ ግልፅነት፣ ተቀባይነት እና ተፈፃሚነት እንዲሁም በተመሳሳይ መልኩ እንዲከናወኑ ለማድረግ ያለመ መሆኑ ተገልጿል።

ከዚህ ባለፈም በረቂቅ ሕግ ዝግጅት ላይ ሲታዩ የነበሩ ችግሮችን ከመሠረቱ መፍታት የሚያስችል ሥርዓት በመዘርጋት የሕግ ሽፋን እንዲኖረው ለማድረግ ያለመ መሆኑም ነው የተገለጸው።

አዋጁ “የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የረቂቅ ሕግ አዘገጃጀት ሥርዓትን ለመወሰን የወጣ አዋጅ ቁጥር 222/2012” በሚል ስም ሥራ ላይ የሚውል መሆኑን የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባዔ ሎሚ በዶ ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ጨፌው ገዳ የኢኮኖሚ ልዩ ዞንን ለመመስረት የቀረበ አዋጅ ላይ ተወያይቶ አጽድቆታል።

ገዳ የኢኮኖሚ ልዩ ዞን በምስራቅ ሸዋ ዞን በሉሜ ወረዳ 13 ቀበሌዎችን እና በአዳማ ከተማ 2 ቀበሌዎችን ያቀፈ ሲሆን፥ 24 ሺህ ሄክታር መሬት ይሸፍናል ተብሏል።

ልዩ የኢኮኖሚ ዞኑ ስራው ሲጠናቀቅ ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ባለሃብቶች ምቹ ሁኔታ ይፈጥራልም ነው የተባለው።

በልዩ የኢኮኖሚ ዞኑ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን፣ ግብርና ማቀነባበሪያ፣ የሳይንስ ቴክኖሎጂ ፓርኮችን፣ ቢሮዎችና የሰራተኞች መኖሪያን ያካተተ ነው።

በተጨማሪም ለህብረተሰቡ አገልግሎት የሚሰጡ ትምህርት ቤት፣ የጤና ተቋማትና ሌሎች አገልግሎት መስጫ ተቋማትን እንደሚያጠቃልልም ተጠቅሷል።

የኢኮኖሚ ዞኑ በቦርድ የሚተዳደር መሆኑን ከኦሮሚያ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.