Fana: At a Speed of Life!

ጠ/ሚ ዐቢይ ከብሄራዊ የዕርቀ ሰላም ኮሚሽን አባላት ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 12 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከብሄራዊ የዕርቀ ሰላም ኮሚሽን አባላት ጋር ተወያይተዋል።

ከተቋቋመ አንድ አመት የሆነው ኮሚሽኑ ባለፈው አንድ አመት ያከናወናቸውን ተግባራት ዝርዝር ሪፖርት አቅርቧል።

በዚህም የማስፈጸም አቅሙን ለማጠናከር የተለያዩ ስራዎች መስራቱን ጠቅሶ፥ በተለይም ከሽግግር ጊዜ ፍትህ ጋር በተያያዘ በሃገር ውስጥ እና በውጭ ሃገራት ልምድ የመቅሰም ስራ መስራቱን ገልጿል።

ኮሚሽኑ የቀጣይ ሶስት አመታት ስትራቴጂክ እቅዱን ለማዘጋጀት ሂደት ላይ ሲሆን፥ ስራውን በተጠናከረ ሁኔታ ለማከናወን ቋሚ ኮሚቴ ማደራጀቱንም አስታውቋል።

የሚሰበስበው መረጃ ሚስጢራዊ ከመሆኑ ጋር ተያይዞም ዳታ ቤዝ እያደራጀ መሆኑን ያነሳው ኮሚሽኑ፥ ከተለያየ ድጋፍ ሰጭ ተቋማት ጋር ያለውን ግንኙነት ማጠናከሩንም ነው የገለጸው።

ከዚህ ባለፈም ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ መስራቱን ጠቁሞ፥ ከሶማሌና ከአፋር በስተቀር ከሁሉም ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች እና የካቢኔ አባላት ጋር መወያየቱንም አስረድቷል።

የኮሚሽኑ የመቋቋሚ አዋጅ ላይ የትርጉም ልዩነት የሚያመጡ ክፍተቶችን ለመሙላትም ደንብ እየተዘጋጀ መሆኑም ተገልጿል።

በሪፖርቱ የኮሚሽኑ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በየሳምንቱ እንዲሁም አጠቃላይ አባላቱ በየወሩ እንደሚሰበሰቡና ስራዎች በየዕለቱ እንደሚከናወኑም ተጠቅሷል።

በአላዛር ታደለ

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.