ሆስፒታሉ የኮሮና ቫይረስ ጽኑ ህሙማንን ለመቀበል የሚያስችለውን ስራ እያጠናቀቀ መሆኑን አስታወቀ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 12 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የኮሮና ቫይረስ ጽኑ ህሙማንን መቀበል የሚያስችለውን የቅድመ ዝግጅት ስራ እያጠናቀቀ መሆኑን አስታወቀ።
ሆስፒታሉ የኮሮና ቫይረስ ድንገት ወደ ሀገር ውስጥ ቢገባ በቫይረሱ የተጠቁ ጽኑ ህሙማንን ተቀብሎ እንዲያስተናግድ በጤና ሚኒስቴር መመረጡ ይታወሳል።
በዚህም የተሟላ የህክምና ማሽን እና አምስት የጽኑ ህሙማን ታካሚዎችን ማስተናገድ የሚችል የጽኑ ህሙማን ማገገሚያ ማዕከል ለይቶ ማዘጋጀቱን ዋና ስራ አስፈጻሚው ዶክተር ታምሩ አሰፋ ገልፀዋል።
ከዚህ ባለፈም በጽኑ ህሙማን ማገገሚያ ማዕከሉ ውስጥ ለሚሰሩ 40 ሰራተኞች በቫይረሱ ህክምና እንዲሁም የቅድመ ጥንቃቄና መከላከያ ስራዎች ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና እየተሰጠ መሆኑንም ተናግረዋል።
በቫይረሱ ዙሪያ ግንዛቤን ለመፍጠር እንዲያስችልም ብሮሸሮችና በራሪ ወረቀቶች በማተም በሆስፒታሉ ለመታከም ለሚመጡትም ሆነ ማህበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም እየተሰራ መሆኑም ነው የተገለፀው።
በአዲስ አበባ ለሚገኙ 13 ሆስፒታሎችም በኢትዮጵያ አየር መንገድና በባቡር ጣቢያዎች ላይ ለሚሰሩ ሰራተኞች 5 ሺህ ለቅድመ መከላከያ የሚያገለግል የአልኮል እጅ ማጽጃ፥ በሆስፒታሉ የፋርማሲ አገልግሎት ክፍል ተመርቶ መሰራጨቱን ከሆስፒታሉ የፌስ ቡክ ገፅ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision