የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ሃይሎች ብሄራዊ የአንድነት መንግስት ለመመስረት ተስማሙ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 12፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ሃይሎች ብሄራዊ የአንድነት መንግስት ለመመስረት ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተገልጿል።
የደቡብ ሱዳን አማጺ ቡድን መሪ ሪካ ማቻር ብሄራዊ የአንድነት መንግስት ለመመስረት ከሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ጋር መስማማታቸውን አስታውቀዋል ።
ማቻር ጉዳዩን አስመልከተው በዛሬው ዕለት በሰጡት መግለጫ ፥ ከሳልቫ ኪር ጋር ብሄራዊ የአንድነት መንግስት መመስረት በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ መግባባት ላይ መድረሳቸውን ገልጸዋል።
ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር በበኩላቸው ብሄራዊ የአንድነት መንግስት ምስረታ ስምምነቱ እውነት መሆኑን አረጋግጠዋል።
በስምምነቱ መረትም ተቀናቃኝ ሃይሎቹ በአውሮፓውያኑ የፊታችን የካቲት 22 ቀን ብሄራዊ የአንድነት መንግስቱን ይመሰርታሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ሃይሎች በፈረንጆቹ 2018 በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም ማስፈን የሚያስችል የሽግግር መንግስት ለመመስረት መስማማታቸው ይታወቃል።
ይሁን እንጂ ተቀናቃኝ ሃይሎች የተለያዩ ምክንያቶችን በማስቀመጥ የሽግግር መንግስት ምስረታ ሂደቱን ሲያራዝሙ መቆየታቸው ይታወሳል።
ምንጭ ፦ ሲጂቲኤን