በጦርነት የተጎዳው ምጣኔ ሐብት እንዲያገግምና የኑሮ ውድነቱ እንዲረጋጋ የኅብረት ሥራ ማኅበራትን ማጠናከር እንደሚገባ ተጠቆመ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) 9ኛው ሀገር አቀፍ የኅብረት ሥራ ኤግዚቢሽን እና ባዛር “የኅብረት ሥራ ግብይት ለሠላምና ለተረጋጋ ገበያ” በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ ነው።
መርሀ- ግብሩ ከዛሬ ጀምሮ እስከ የካቲት 7 ይቆያልም የተባለ ሲሆን የመርሃ ግብሩ አካል የሆነ ሲምፖዚየም በሸራተን አዲስ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
የኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽነር ተወካይ ብርሃኑ ዱፌራ ÷ የግብይት ሥርዓቱን በማዘመንና የኅብረተሰቡን የፋይናንስ ንቃተ ህሊና በማሳደግ ማኅበራት ሃላፊነት ሊወጡ ይገባል ብለዋል።
የኑሮ ውድነቱ በተለይ በከተማው ነዋሪው ላይ ተፅዕኖ በማሳደር ላይ መሆኑ በሲምፖዚየሙ የተነሳ ሲሆን ገበያውን ለማረጋጋት መሥራት ይገባል ተብሏል፡፡
በጦርነቱ የተጎዳው ምጣኔ ሐብት እንዲያገግም ለማድረግና ገበያውን ለማረጋጋት የተሻለ የግብይት ሥርዓት እንደሚያስፈልግ ጠቁመው አቅምን ማጠናከር እንደሚገባ አክለዋል።
የግብርና ሚኒስትር ተወካዩ አቶ ግርማ በቀለ በበኩላቸው ኅብረት ሥራ ማኅበራት የአርሶና አርብቶ አደሩን ሕይወት ለማሻሻልና የግብይት ሁኔታውን ለማዘመን ሃላፊነት አለባቸውም ነው ያሉት።
በአፈወርቅ እያዩና ቅድስት ተስፋዬ