Fana: At a Speed of Life!

የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ ተመድ ለክልሉ ሕዝብ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቀረቡ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ጨምሮ ሌሎች ዓለም አቀፍ ረጂ ድርጅቶች በየጊዜው ጦርነት እየተከፈተበት የሚገኘውን የአፋር ሕዝብ እንዲደግፉ ጥሪ አቀረቡ።

በፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ምክትል ዋና ጸሐፊ አሚና መሐመድ የተመራ የልዑካን ቡድን ከርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ እና ከተለያዩ የጎሳ መሪዎች ጋር ወቅታዊ የክልሉን ሁኔታ በተመለከተ ውይይት አድርጓል።

ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ አሸባሪው ህወሓት የክልሉን ድንበር ተሻግሮ በአሁኑ ወቅት በአምስት ወረዳዎች ላይ ጦርነት መክፈቱን ገልፀዋል።

ጦርነት ከተከፈተባቸው ወረዳዎች ሦስቱ ጦር ያልሰፈረባቸው የንፁሀን መኖሪያ መንደሮች መሆናቸውን እና ጥቃቱም ንፁሀን ዜጎች ላይ ያነጣጠረ መሆኑን ተናግረዋል።

ተመድን ጨምሮ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት አፋር ክልል መጥተው ሰብአዊ ድጋፍ ወደ ትግራይ ክልል ስለሚደርስበት መንገድ ከመነጋገር ባሻገር ወረራ የተፈፀመበትን የአፋር ሕዝብ ስለመርዳት እንዲያስቡም ጠይቀዋል።

አፋር ሰብአዊ እርዳታዎች ወደ ትግራይ እንዲሄድ መንገድ ከማመቻቸት ጀምሮ ማከማቻ መጋዘኖች እንዲኖሩ ያሉት ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ፣ የትግራይ ሕዝብም ጠላት የሆነው አሸባሪው ህወሓት ግን የተከፈቱ መንገዶች ላይም ጦርነት እንደከፈተ ገልጸዋል።

ተመድ እርዳታ ጭነው ወደ ትግራይ ሄደው ያልተመለሱ መኪኖቹ ምን እየሠሩ እንደሆነ እና ዕርዳታዎችም ለጦርነት ዓላማ ሳይሆን ለንፁሀን ዜጎች ስለመድረሳቸው ሊያጣራ ይገባልም ብለዋል።

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ÷ የአፋር ክልል ለሀገር ትልቅ ዋጋ እየከፈለ ያለ መሆኑን ገልጸው ለዚህም ምስጋና ይገባዋል ብለዋል።

እንደ ኢቢሲ ዘገባ የተመድ ምክትል ዋና ጸሐፊ አሚና መሐመድ በበኩላቸው፣ ጦርነቱ በሚቆምበት እና ሰላማዊ ውይይቶች በሚኖሩበት ሁኔታ ላይ ይሠራል ብለዋል።

ሰብአዊ ድጋፎች ጦርነት ባለበት በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል ለሚገኙ ንፁሀን እንዲደርስ እንሠራለን ሲሉ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.