በድርቅ መቋቋምና ዘላቂ የአርብቶ አደሮች ኑሮ ማሻሻያ ላይ ያተኮረ ውይይት ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በግብርና ሚኒስቴር የድርቅ መቋቋምና ዘላቂ የአርብቶ አደር ኑሮ ማሻሻያ ፕሮግራም የተሰሩ ስራዎች የ6 ወር የእቅድ አፈጻጸም ግምገማ ተካሄደ፡፡
በግብርና ሚኒስቴር የድርቅ መቋቋምና ዘላቂ የአርብቶ አደር ኑሮ ማሻሻያ ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ጀማል አሊዪ÷ የአርብቶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ማሳደግ እና የአኗኗር ዘይቤ ማሻሻል የፕሮጀክቱ ዋና ዓላማ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አስተባባሪው ፕሮግራሙ የአርብቶ አደሩን ማህበረሰብ ድርቅ ከሚያመጣው ተፅዕኖ መከላከልና በዝናብ ላይ ያለውን ጥገኝነት በመቀነስ በእንሰሳት ምርታማ እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ፕሮጀክቱ በተፈጥሮ ሃብት አያያዝ፣ የገበያ ተደራሽነትና ንግድ፣ የኑሮ ማሻሻያ ድጋፍ እንዲሁም ሰብዓዊና ተቋማዊ አቅም ግንባታ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራም ተመላክቷል፡፡
በዚህም የከርሰ ምድር ውሃ ሃብት ልማት ፣ የግጦሽ ሳር ልማት፣ የእንስሳት ገበያ መሰረተ ልማት፣ የእንስሳት ጤና ማዕከላትና የመጋቢ መንገዶች ግንባታ የሚጠቀሱ መሆናቸውንም አብራርተዋል፡፡
ፕሮግራሙ በሁሉም የትግበራ ምዕራፎቹ የስርዓተ ጾታ አካታችነትን በልዩ ትኩረት በመመልከት ሴቶች፣ ህጻናትና አቅመ ደካሞችን በማህበረሰብ ተሳትፎ ተጠቃሚ እያደረገ እንደሚገኝ አቶ ጀማል አስረድተዋል፡፡
በመድረኩ የሶማሌ፣ የአፋር፣ የኦሮሚያና የደቡብ ክልሎች የአፈጻጸም ሪፖርት የቀረበ ሲሆን÷ በዝናብ እጥረት ምክንያት ከባድ ድርቅ መከሰት፣ የሰላም መደፍረስ፣ የግንባታ መዘግየትና የግንባታ እቃዎች ዋጋ መናር በእቅድ አፈጻጸሙ የታዩ ተግዳሮቶች መሆናቸው መጠቀሱን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!