Fana: At a Speed of Life!

በአዲስ አበባ የጤና ባለሙያዎች ከየካቲት 1 ቀን ጀምሮ የሙያ ማሻሻያ ስልጠና መውሰድ እንዳለባቸው ባለስልጣኑ አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የጤና ባለሙያዎች ከየካቲት 1 ቀን ጀምሮ ተከታታይ የሙያ ማሻሻያ (CPD) ስልጠና መውሰድ እንዳለባቸው የአዲስ አበባ ምግብ መድሃኒት ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን አስታወቀ፡፡
ባለስልጣኑ ከጤና ሚኒስቴር በተሰጠው አቅጣጫ መሰረት ማንኛውም የጤና ባለሙያ ከየካቲት 1 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ የተከታታይ የሙያ ማሻሻያ (CPD) ስልጠና መውሰድ እንዳለበት አሳስቧል፡፡
በባለስልጣኑ የጤና ተቋማትና ባለሙያዎች ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አምደየሱስ አድነው እንደገለጹት፥ የጤና ባለሙያዎች ተከታታይ የሙያ ማሻሻያ ዋና ዓላማ የጤና ባለሙያዎች ዕውቀታቸውን በማሳደግ ለህብረተሰቡ ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ነው፡፡
በተጨማሪ የጤና ባለሙያዎች እየተፈተኑ ራሳቸውን እንዲያውቁ ለማድረግ ያለመ ነው ማለታቸውን ከአዲስ አበባ ምግብ መድሃኒት ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

 

ከተቋማት ከሚሰጠው ስልጠና በተጨማሪ በኦንላይን መንገድ ተጠቅሞ ስልጠናውን ለመውሰድ አማራጭ መኖሩን የጠቆሙት አቶ አምደየሱስ፥ በዚህ ዓመት ስልጠናውን ያልወሰዱ ባለሙያዎች በሚቀጥለው ዓመት ክሬዲት ሀወሩ እየጨመረ ስለሚሄድ ከወዲሁ የስራና የሙያ ማሻሻያ (CPD) ስልጠና ለመውሰድ ዝግጁ መሆን ይገባቸዋል ብለዋል፡፡
የባለሙያዎች የሙያ ምዝገባና ፈቃድ አሰጣጥ ዳይሬክተር ሙሉጌታ ወንድሜነህ በበኩላቸው፥ የስራና የሙያ ፈቃድ ለማደስ ከሚያስፈልጉ መስፈርቶች በተጨማሪ ተከታታይ የሙያ ማጎልበቻ (CPD) ስልጠና ማንኛውም የጤና ባለሙያ መውሰድ እንዳለበት የጤና ሚኒስቴር ደንብና መመሪያ ማውጣቱን አብራርተዋል፡፡
እስካሁን ተከታታይ የሙያ ማጎልበቻ ስልጠናው ያልተጀመረበት ምክንያት ሁሉም ባለሙያዎች ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለማድረግና ለባለሙያዎች የስራ ሙያ ማጎልበቻ ስልጠና የሚሰጡ ተቋማት ዝግጁ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ሲባል መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ስልጠናውን የሚሰጡ ተቋማት መኖራቸውንና የጀመሩም እንዳሉ ጠቁመው፥ ከየካቲት 1 ቀን ጀምሮ ማንኛውም የጤና ባለሙያና COC እየተሰጣቸው ያሉ ዘጠኝ የሙያ ዘርፎችና ስፔሻሊስቶችም አብረው ተከታታይ የሙያ ማጎልበቻ ስልጠናውን እንዲወስዱ አሳስበዋል፡፡
በዓመት 30 ዩኒት(CU) መውሰድ እንደሚገባ አስገንዝበው ባለሙያዎችም ይህን አሟልተው ሲመጡ የስራና የሙያ ፈቃድ ማደስ እንደሚችሉ ገልፀዋል። ይህን አሟልተው ካልመጡ ግን ጊዚያዊ የስራና የሙያ ፈቃድ በመስጠት እስከ ሰኔ 30 ቀን 2014ዓ.ም ግን ተከታታይ የሙያ ማጎልበቻ ስልጠና የሚጠበቅባቸውን 30 ዩኒት ሲያሟሉ ቋሚ የስራና የሙያ ፈቃድ ለ3 ዓመት እንደሚሰጥ አብራርተዋል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.