Fana: At a Speed of Life!

ሃይማኖቶች የመንግስትን ድንበር ሳያልፉ፤ መንግስትም የእምነቶችን ድንበር ሳይሻገር ተቋማዊ በሆነ መልኩ እንደጋገፋለን – ወ/ሮ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሃይማኖቶች የመንግስትን ድንበር ሳያልፉ፤ መንግስትም የእምነቶችን ድንበር ሳይሻገር ተቋማዊ በሆነ መልኩ እንደሚደጋገፉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታወቁ።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤቱ አባላት በስድስት ወራት የአስፈፃሚው ሪፖርት ላይ ላነሷቸው ጥያቄና አስተያየቶች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ከሰላምና ፀጥታ ጉዳዮች እንዲሁም ከሃይማኖት ጉዳዮች ጋር የተነሱ ጉዳዮችን በተመለከተም እንዲሁ አብራርተዋል።

ከተማዋ ተጠንስሶላት ከነበረው እቅድ አንፃር ሲታይ የተሳካ የፀጥታ ጥበቃ ስራ መሰራቱና ነገር ግን ወንጀልን ከማስቀረትና የህግ የበላይነት ከማረጋገጥ አንፃር በርካታ የሚቀሩ ስራዎች እንዳሉ ነው የጠቆሙት።

የፀጥታ መዋቅሩን በተመለከተ እጅግ የሚመሰገን ስራ መስራቱንና በተለይ አንዳንዶች ወንጀለኛ ለመያዝ ሲሉ ቦንብ ፈንድቶባቸውና ተደብድበው እስከ ሞት የደረሰ መስዋዕትነት በመክፈላቸው ምስጋና የሚገባቸው ናቸው ብለዋል።

የከተማውን ፖሊስ ከ1997 በኋላ የተጠሪነት ችግር እንዳለበት አውስተው፥ በተለይ ከተማዋ ትልቅ እንደመሆኗ መጠን ፖሊስ ሪፎርም ማድረግ ይኖርበታል ነው ያሉት፡፡ በቂ የስልጠና ተቋም፣ የሰው ሃይልና የሎጂስቲክስ አቅርቦት ሊኖረው ይገባል ባይ ናቸው፡፡

ከሃይማኖትና ከመንግስት ግንኙነት አንፃር ሰፋ ያለ ማብራርያ ለምክር ቤቱ ያቀረቡት ወ/ሮ አዳነች፥ አንዳንድ ሰዎች የለውጡ መንግስት ለሃይማኖት የተዛባ አተያይ እንዳለው አድርገው ያቀርባሉ፤ ሆኖም ግን እውነታው ተቃራኒ ነው ብለዋል።

“እኛ በየትኛውም ሃይማኖት ውስጥ የወከልነው ሰው የለም” ያሉት ከንቲባዋ፥ “በእምነቶች ውስጥ ያደራጀነው ሶሻል ግሩፕም የለም፤ የእኛ ግንኙነት ፍፁም ተቋማዊና የሴኩላሪዝም መርህን የማይጥስ ነው” ብለዋል፡፡

“በሰላም እና ሃገራዊ በሆኑ ጉዳዮች የምንተባበርባቸው አጀንዳዎች አሉ፤ ሃይማኖቶች የመንግስትን ድንበር ሳያልፉ፤ መንግስትም የእምነቶችን ድንበር ሳይሻገር ተቋማዊ በሆነ መልኩ እንደጋገፋለን” ሲሉ አብራርተዋል።

“መንግስት የሆነው ሁሉንም እኩል እንድንመራና እንድናስተባብር ነው” ያሉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፥ የግል እምነት የየራሳችን ቢኖረንም እንኳን ሁሉንም በእኩልነትና በፍትሃዊነት እናስተናግዳለን፤ ይህንንም ነው የምንቀጥለው” በማለት አስረድተዋል፡፡

ነገር ግን የሃገር ቅርስ እና ገፅታ የሆኑትን ጠቃሚ በሆነ መንገድ ደግሞ በመደገፍ ገፅታው ሃገራችንን በሚጠቅም መልኩ እንዲገለፅ እንደ መንግስት ጥረት ይደረጋል ብለዋል፡፡

ባለፉት ሶስት አመታት ውስጥ የሃይማኖት ተቋማቱ በጋበዙን ቦታ እንደ መንግስት በአክብሮትና በትህትና ተገኝተናል ነው ያሉት።

በተለይ ሀይማኖታዊ በዓላት በሚከበሩበት ቦታዎች ስጦታዎችን በመስጠትና ፅዳት በማድረግ መከባበር፣ መተሳሰብና አብሮነት እንዲኖር ትኩረት ተሰጥቶ መሰራቱን ጠቁመዋል ፡፡ አክለውም በኮቪድ ወቅት የእምነት ተቋማት በጋራ መፀለያቸውንና በብዙ መንገዶች በትብብር መስራታቸውን ተናግረዋል።

ከመሬት ጋር ተያይዞ ለሚነሳው ጥያቄ ሁሉም የእምነት ተቋማት በጋራ የፈረሙበት ባለፉት ሶስት አመታት 2014ን ሳይጨምር በመስተዳድሩ የተሰጡ ቦታዎችን በተመለከተ ሲያስረዱም፥ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን 89 ቦታዎች የመስጠት እና በአራት ኪሎ የሚገኘውን ባለመንትያ ህንፃ የማስመለስ ስራ መከናወኑን ጠቁመዋል። ይህም ስፋቱ ከ1 ሚሊየን ካሬ ሜትር በላይ መሆኑን ነው ያመለከቱት።

በተመሳሳይ ለእስልምና እምነት 85 ቦታዎች ማለትም 260 ሺህ 968 ካሬ ሜትር፣ ለወንጌላውያን አማኞች በጠቅላላ 47 ቦታዎች ወይም 98 ሺህ 290 ካሬ ሜትር፣ ለኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሶስት ቦታዎች በስፋት 700 ካሬ ሜትር እና ለሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ሶስት ቦታዎች በስፋት 6 ሺህ 812 ካሬ ሜትር ቦታ መሰጠቱን ገልፀዋል።

ይህንንም ስራ ሁሉም የእምነቱ ተወካዮች ተወያይተው ባፀደቁበት መልኩ ማስተላለፍ መቻሉን በማንሳት፥ ይህንን ማድረግ የቻለ አስተዳደር ከዚህ በፊት አልነበረም ማለታቸውን ነው ከከንቲባ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለከተው።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.