Fana: At a Speed of Life!

የአፍሪካ ኅብረት ራሱን በጥልቀት በመፈተሽ አህጉሪቱንና ዜጎቿን ከችግር የማውጣት ኃላፊነት አለበት – ምሁራን

አዲስ አበባ፣ የካቲት 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ ኅብረት ራሱን ቆም ብሎ በጥልቀት በመፈተሽ ዜጎቿና አህጉሪቱን ከችግር የማውጣት ኃላፊነትና ግዴታ አለበት ሲሉ ምሁራን ገለጹ፡፡

የአፍሪካ ኅብረት የበለፀገች፣ ሰላምና ደህንነቷ የተረጋገጠ፣ በራሷ ዜጎች የምትመራ በዓለም አቀፍ መድረኮች ተሰሚነት ያላት አህጉርን እውን ለማድረግ በአጀንዳ 2063 አስቀምጧል።

አጀንዳ 2063 አህጉሪቷ የተፈጥሮ ሀብቷን ከሰው ሀይሏ ጋር በማቀናጀት በሁሉም መስኮች የበለፀገችና የዘመነች ማድረግን ተቀዳሚ ዓላማው ያደረገ ነው።

ይህ አጀንዳ 2063 ታዲያ በተለያዩ መስኮችና አቅዶች የተከፋፈለ ሲሆን ፥ የመጨረሻ ግቡ የበለፀገች ቀጠናዊ ውህደት የፈጠረች ሰላምና ፀጥታዋ የተረጋገጠላት፣ በራሷ ልጆች የምትመራ እና በዓለም አደባባይ በጠንካራ ልጆቿ የተወከለች አህጉርን መፍጠር ታሳቢ ያደረገ ነው።

ይህ እቅድ በረጅም፣ በመካከለኛ እና በአጭር ጊዜ የተከፋፈለ ጭምር ነው።

ከጣቢያችን ጋር ቆይታ ያደረጉት የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር እና የፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኙ ዶክተር ንጉስ በላይ እንደሚናገሩት፥ ኅብረቱ ካስቀመጣቸው የአጭር ጊዜ እቅዶች መካከል በ2020 በአህጉሪቱ የጦር መሳሪያ ድምፅ እንዳይሰማ ማድረግ የሚለው አቅድ አለመተግበሩን ነው የሚያነሱት።

የባህር ዳር ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስና የዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህሩ ዶክተር በውቀቱ ድረስ በበኩላቸው እንዲሁ፥ ኅብረቱ በ2020 አንድም የጦር መሳሪያ ድምፅ አንዳይሰማ የሚለው እቅዱ በመክሸፉም አሁን ላይ በአህጉሪቱ ከፍተኛ የሰላም እጦት መኖሩን ይገልፃሉ።

በኢኮኖሚው ረገድም ቢሆን የአፍሪካ ኅብረት በ2020 አሳካዋለሁ ብሎ ያስቀመጠው እቅድ ቢኖርም መሬት ላይ ወርዶ አህጉሪቱን ከልመና፥ ዜጎችንም የሰው እጅ ከማየት ሊታደግ አልቻለም ይላሉ ምሁራኑ።

ከዚህ ባለፈ በውሳኔ ሰጪነት ላይም አፍረካዊ የምዕራባውያን አሉታዊ ጫና እንዳለባት ተናግረዋል።

በተለይም ከመፈንቅለ መንግስት ጋር በተያያዘ ያለው ቸልተኝነት አሳሳቢ እንደሆነ ነው ዶክተር ንጉስ የሚናገሩት።

እነዚህን ችግሮች ለመፍታት አሁንም ኅብረቱ ራሱን ቆም ብሎ በጥልቀት በመፈተሽ ዜጎቿንና አህጉሪቱን ከችግር የማውጣት ሃላፊነትና ግዴታ አለበት ነው የምሁራኑ የሚሉት።

በመሃመድ አሊ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.