Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለዓለም አቀፍ ውድድር ራሱን ሊያዘጋጅ ይገባል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያስገነባውን አዲስ ህንጻ በዛሬው ዕለት መርቀው ከፍተዋል።
 
በምረቃ መርሃ ግብሩ የተለያዩ ሚኒስትሮች፣ የባንኩ የስራ ሃላፊዎች፣ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት፣ የባንኩ የሥራ ኃላፊዎች፣ የባንኩ ደንበኞች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተኝተዋል።

 
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 80ኛ ዓመት የምስረታ በዓል እና ለአዲሱ ዋና መስሪያ ቤት ህንጻ ምረቃ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
 
የምንፈልጋት ኢትዮጵያ ትናንት የለፉላትን የምታስታውስ፣ ዛሬ የሚሰሩላትን የምታመሰግን፣ ለነገዎች አርዓያ መፍጠር የምትችልን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፥ ባንኩ ይህን ያስታወሰን በመሆኑ ምስጋና ይገባዋል ብለዋል፡፡
 
የባንኩ ተግባር ኢትዮጵያ ተቋም መገንባት እንደምትችል እና ለቀጣይ ትውልድ የማስተላለፍ ልምዱ እንዳላት ማሳያ ነው ሲሉም አውስተዋል፡፡
ለኢትዮጵያ የፋይናንስ ስርዓት ታሪክ የሆነው ባንኩን በጋራ የልደት በዓሉን ለማክበር በመገኘቴም ደስተኛ ነኝ ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
 
ባንኩ በዘርፉ ካለው አጠቃላይ ካለው ሃብት ከ62 በመቶ በላይ የሚይዝ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፥ ይህም ባንኩን የአገሪቱ የፋይናንስ ዋርካ ያስብለዋል ነው ያሉት፡፡
 
ባንኩ በ80 ዓመት ጉዞው በርካታ ተግዳሮቶች ማሳለፉን በማንሳትም፥ እስካሁን ላበረከተው አስተዋጽኦ አመስግነዋል፡፡
 
ለኢትዮጵያ ተቋማትን እያፈረሱ መገንባት አያዋጣም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ መልካሙን ነገር ከትናንት ተምሮ የተበላሸውን በማስተካከል እና ዘመን የሚዋጅ ሀሳብ በማከል ማስቀጠል ያስፈላጋል ብለዋል፡፡
 
በቀጣይም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ራሱን ለዓለም አቀፍ ውድድር ሊያዘጋጅ እንደሚገባ ነው የጠቆሙት፡፡
 
በፋይናንስ ዘርፉ ላለፉት 30 ዓመታት ምንም የውጭ ባንክ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ ከለላ ተደርጎ የነበረው ስርዓት በዚህ ሁኔታ እንደማይቀጥል ጠቁመው፥ የኢትዮጵያ ባንኮች በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚገኙ ባንኮች ጋር በአገልግሎት አሰጣጥ እና በሌሎች ዘርፎች ለመፎካከር እራሳቸውን ማዘመን እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
 
ለሌሎች ዋርካ ብለው የገለፁት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለዚህ ውድድር ብቁ ሆኖ መጠበቅ እንዳለበት ነው የተናገሩት።
 
 
በመላኩ ገድፍ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.