Fana: At a Speed of Life!

የመድሀኒቶችን የጎንዮሽ ጉዳትና የአጠቃቀም ችግር ለማቃለል 6 ማዕከላት ተቋቋሙ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 13፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የመድኃኒቶችን የጎንዮሽ ጉዳትና የአጠቃቀም ችግር ማቃለል የሚያስችሉ ስድስት ማዕከላት ማቋቋሙን የኢትዮጵያ የምግብና መድሃኒት ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

በኢትዮጵያ ከመድኃኒት አጠቃቀም ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ ችግሮችን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን በባለስልጣኑ ቁጥጥር የሚደረግባቸው ምርቶች ደህንነት ዳይሬክተር ወይዘሮ አስናቀች ዓለሙ አስታውቀዋል፡፡

ከጥረቶቹ መካከል በተለያዩ አካባቢዎች የመድኃኒትን የጎንዮሽ ጉዳትና የአጠቃቀም ችግር ለማቃለል የሚሰሩ ማዕከላትን ማደራጀት ዋናው ተግባር መሆኑን ጠቅሰዋል።

አንዳንድ ጊዜም መድሃኒቶች በተገቢው መንገድ ካልተወሰዱ የመላመድ ባህሪ ስለሚኖራቸው ፈዋሽነታቸውን በማጣት የጎንዮሽ ጉዳት ሊያስከትሉ እንደሚችሉ ጠቁመው፥ ማዕከላቱ ለችግሩ የሚሆን መፍትሄ እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል።

ስለሆነም እነዚህን ችግሮች ለመፍታት በአዲስ አበባ፣ በጅማ፣ በሐረር፣ በሐዋሳ፣ በጎንደርና መቐለ በሚገኙ ሆስፒታሎች የተቋቋሙ 6 ማዕከላት ከጥቅምት 2012 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ስራ መግባታቸውን አስረድተዋል።

ማዕከላቱ መድሃኒት የሚወስዱ ሰዎች የሚያጋጥማቸውን የመድሃኒት የጎንዮሽ ጉዳት እንዲያውቁ የሚያስችሉ ናቸው ብለዋል።

ከተቋቋሙ በኋላ 6 ሺህ 800 ጥቆማዎች ከህብረተሰቡ መድረሳቸውን ገልጸው ከዚህ ጋር ተያይዞ ጥቆማ የተሰጠባቸው መድሃኒቶች እንዲቀየሩና እንዲቀሩ ተደርገዋልም ነው ያሉት፡፡

በሃገር ውስጥ የሚመረቱ መድኃኒቶች የጎንዮሽ ጉዳት እንዳያስከትሉ ከምርት ጀምሮ ተጠቃሚው ዘንድ እስከሚደርሱ ድረስ ደህንነታቸው ሊጠበቅ ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.