በአሜሪካ ምክር ቤት የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ የተላለፈው ኤች አር 6600 የውሳኔ ኃሳብ ወገንተኝነት የታየበት መሆኑ ተገለፀ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 7፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሜሪካ ምክር ቤት የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ በቅርቡ ያሳለፈው ኤች አር 6600 የተሰኘው የውሳኔ ኃሳብ ትክክል ያልሆነና ወገንኘትነት የተንጸባረቀበት ነው ሲል የኢትዮጵያ አሜሪካዊያን ዜጎች ምክር ቤት ገለጸ።
ባሳለፍነው ሣምንት የአሜሪካው ምክር ቤት የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ በኢትዮጵያ የሰላምና የዴሞክራሲ ግንባታ ለመደገፍ በሚል ኤች አር 6600 የተሰኘ የውሳኔ ኃሳብ አሳልፏል።
ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያ አሜሪካዊያን ዜጎች ምክር ቤት ሊቀመንበር ዲያቆን ዮሴፍ ተፈሪ የውሳኔ ኃሳቡ ሕወሃትን ለማትረፍ የሚፈልጉ ወገኖች ያዘጋጁት ነው ብለዋል።
የውሳኔ ኃሳቡ ምንም እንኳን ኢትዮጵያን ለማረጋጋትና በኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ለማስፈን የሚል ስያሜ ቢሰጠውም ዋነኛ ዓላማው በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማድረግ መሆኑን ገልጸዋል።
የውሳኔ ኃሳቡን የፃፉትና በዋናነት የደገፉት የውጭ ጉዳይ ኮሚቴው ሰብሳቢ ግሬገሪ ሚክስን ጨምሮ ሌሎች ግለሰቦች ለሕወሃት ወገንተኝነታቸውን የሚያሳዩ መሆናቸውን አንስተዋል።
የተዘጋጀው ኤች አር 6600 የውሳኔ ኃሳብም ሕወሃትን ለመደገፍ የተዘጋጀ እቅድ መሆኑን ጠቁመዋል።
የውሳኔ ኃሳቡን ያሳለፉት ሰዎች ከሕወሃት ተከራካሪዎች (ሎቢስቶች) ጋር ከፍተኛ ቁርኝት እንዳላቸውና የገንዘብም ድጋፍ እንደሚደረግላቸው መረጃዎች እየወጡ መሆኑን ጠቁመዋል።
የውሳኔ ኃሳቡ የኢትዮጵያን ተጨባጭ መረጃዎች ያላማከለና ለአንድ ወገን ያደላ መሆኑን ገልጸው፥ በውሳኔ ኃሳቡ የተካተቱት ኃሳቦች ሚዛናዊ ያልሆኑ፣ በስሜታዊነትና ከሕወሃት ጋር ባለ ወዳጅነት የተዘጋጀ መሆኑንም አስረድተዋል።
የውሳኔ ኃሳቡ አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግነኙነት የሚያሻክር በመሆኑ፥ የሚመሩት ምክር ቤትም የውሳኔ ኃሳቡን በመቃወም እንቅስቃሴ ጀምሯል ብለዋል።
ምክር ቤቱ 10 አንቀፅ ያለው የተቃውሞ ደብደቤ አዘጋጅቶ ለሁሉም የአሜሪካ ኮንግረስና የሴኔት አባላት መላኩን ተናግረዋል።
ለ150 ሚሊየን ሕዝብ ሊደረስ የሚችል የተቃውሞ ዝርዝር መረጃም በመገናኛ ብዙኃን እንደሚሰራጭ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!