ለሶማሌ ክልል ጤና ቢሮ በ900 ሺህ ዶላር ወጪ የተገዛ የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 7፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አርት ፋውንዴሽን ከግሎባል ሜዲካል ኤድ ጋር በመተባበር በ900 ሺህ ዶላር ወጪ የተገዛ የተለያየ የህክምና ቁሳቁስ ለሶማሌ ክልል ጤና ቢሮ ለግሷል፡፡
በርክክብ መርሃ ግብሩ የክልሉ ማህበራዊ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ፣ የክልሉ ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ቢሮ ምክትል ኃላፊና ሌሎች የስራ ሀላፊዎች በተገኙበት÷ የክልሉ ጤና ቢሮ ለአርት ፋውንዴሽንና ግሎባል ሜዲካል ኤድ የእውቅና የምስክር ወረቀት አበርክቷል፡፡
የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሙሴ አሕመድ÷ የተለያዩ የህክምና ቁሳቁሶችን እንደተረከቡ ገልጸው ከእነዚህም መካከል ለኩላሊት እጥበት የሚያገለግል የዲያለሲስ ማሽን፣ አልጋዎች፣ ዊልቸርና የተለያዩ የሜዲካል እቃዎች እንደሚገኙበት ተናግረዋል፡፡
ድጋፉ በማህበር ከተደራጁ የግብረ ሰናይ ድርጅቶች ሲገኝ ይሄ የመጀመሪያው መሆኑን የገለፁት ዶክተር ሙሴ÷ እንደዚህ አይነት ድጋፎች በውጪ በሚገኙ የክልሉ ተወላጅ ዳያስፖራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
የክልሉ ተወላጅ ዳያስፖራዎች በይበልጥ በአሁኑ ሰአት በክልሉ የተፈጠረውን ድርቅ በመገንዘብ ከህዝባቸው ጎን በመቆም ድጋፍ እንዲያደርጉም ነው የጠየቁት፡፡
የአርት ፋውንዴሽን ኃላፊ ወይዘሮ ነስቲሃ አሊ በበኩላቸዉ÷ እንደዚህ አይነት ድጋፎችን ከዚህ በፊትም በሶማሊያ፣ በኬኒያ፣ በሶማሊላንድና በጁባላንድ ማድረጋቸውን ገልፀው÷ በሶማሌ ክልል ድጋፍ ሲያደርጉ የመጀመሪያቸው መሆኑን የክልሉ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት ዘግቧል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!