በጦርነቱ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች እየተደረገ ያለው የስነ-ልቦና ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል
አዲስ አበባ፣ የካቲት 7፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በጦርነቱ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች እየተደረገ ያለው የስነ-ልቦና እና ማህበራዊ ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።
የህወሓት ሽብር ቡድን በአፋርና አማራ ክልሎች በወረራ በቆየባቸው አካባቢዎች በኢኮኖሚ ላይ ካሳደረው አሉታዊ ተጽእኖ ባሻገር በማኅበረሰቡ ላይ ከፍተኛ የሆነ ማኅበራዊና ሥነ-ልቦናዊ ቀውስ አስከትሏል፡፡
ከዚህ አኳያ የጤና ሚኒስቴር በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች የስነ-ልቦና ድጋፍ እንዲያገኙ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን አስታውቋል፡፡
በዛሬው ዕለትም የዚሁ ስራ አካል የሆነና በጦርነቱ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች የሥነ-ልቦና፣ ማኅበራዊና የአእምሮ ጤና ድጋፍ መስጠት የሚያስችል የአሰልጣኞች ሥልጠና በአፍሪካ የአመራር ልህቀት አካዳሚ ተጀምሯል።
የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በዚህ ወቅት ስልጠናው በዋናነት ከችግሩ ስፋት አንጻር ሁሉንም ተጎጂዎች ተደራሽ ማድረግን ያለመ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ስልጠናው በዋናነት የጤና ባለሙያዎችን፣ ጾታዊና ህጻናት ጥቃትን ለመከላከል የሚሰሩ አካላትን እንዲሁም የማህበረሰብ መሪዎችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ መዘጋጀቱን አብራርተዋል፡፡
ሚኒስቴሩ ከዚህ ቀደም በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች የስነ-ልቦና እና ማህበራዊ ድጋፍ እንዲያገኙ ሲሰራ መቆየቱን ያብራሩት ሚኒስትሯ÷በዚህም ባለፉት 4 ወራት ብቻ ከ42 ሺህ 842 በላይ ለሚሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሥነ-ልቦናና የአእምሮ ጤና ሕክምና ድጋፍ እንደተደረገላቸው ጠቁመዋል።
የአንድ ማዕከል አገልግሎት በማቋቋም ጾታዊ ጥቃት ለደረሰባቸው ወገኖች የሕክምና ድጋፍ ለመስጠት እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ድኤታ ወይዘሮ አየለች እሸቴ በበኩላቸው÷ በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች አስፈላጊውን ድጋፍ እዲያገኙ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በጦርነቱ ብቻ ሳይሆን በድርቅ ለተጎዱ የማኅበረሰብ ክፍሎችም የሥነ-ልቦና ድጋፍ ለማድረግ እየሰተራ መሆኑን ገልጸው÷ለዚህም በተመድ የሕጻናት አድን ድርጅት (ዩኒሴፍ) በኢትዮጵያ ተጠሪ ዳይሬክተር ጂያን ፍራንኮ፤ ጉዳት ለደረሰባቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች የሥነ-ልቦና ድጋፍ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በስልጠናው ከአማራ፣ አፋር፣ ኦሮሚያና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎችና ከፌደራል የመጡ 270 የዘርፉ ባለሙያዎች እየተሳተፉ ሲሆን÷ ከዛሬ ጀምሮ ለተከታታይ 5 ቀናት የሚቆይ ይሆናል።