ብሄራዊ የበጎ ፈቃድ የማህበረሰብ አገልግሎት ፕሮግራም ማብሰሪያ ስነ ስርዓት እሁድ ይካሄዳል
አዲስ አበባ ፣ የካቲት 13 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ብሄራዊ የበጎ ፈቃድ የማህበረሰብ አገልግሎት ፕሮግራም ማብሰሪያ ስነ ስርዓት የፊታችን እሁድ ይካሄዳል።
ፕሮግራሙ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት ነው የሚካሄደው።
የሰላም ሚኒስቴር መርሃ ግብሩን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ፥ ወጣቶች በሰለጠኑበት የሙያ ዘርፍ ፍላጎት ባሳዩባቸው ዘርፎች ከተወለዱበት አካባቢ ርቀው በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች አገልግሎት እንደሚሰጡ አስታውቋል።
በጎ ፈቃደኛ ወጣቶቹ አብሮ የመኖር የህይወት ክህሎታቸውን በማዳበር ወደስራ የመግባት እድላቸውን ያሰፉበታል ተብሎም ይጠበቃል።
እስካሁን ከ100 ሺህ በላይ ለሆኑ ወጣቶች ምዝገባ እና የስልጠና ሞጁል መዘጋጀቱም ነው የተገለጸው።
በበጎ ፈቃድ መርሃ ግብሩ የመጀመሪያ ዙር የሚሳተፉ ከ2 ሺህ በላይ ወጣቶች ዝግጅት አጠናቀዋልም ነው የተባለው።
ወጣቱን ለማነሳሳትም አርዓያ እና አነቃቂ መሆን የሚችሉ የበጎ አድራጊ አምባሳደሮች ተመርጠዋል።
በዚህም ሲስተር ዘቢደር ዘውዴ፣ ፓስተር ዮናታን አክሊሉ፣ ዑስታዝ ያሲን ኑሩ እና ወይዘሮ ፊልሰን አብዱላሂ አምባሳደር ሆነው ተመርጠዋል።
ወጣቶቹ በሄዱበት አካባቢ ማህበረሰቡ ድጋፍ በሚያስፈልገው ቦታ ሁሉ ያገለግላሉ ተብሏል።
በጎ ፈቃደኞቹ አገልግሎቱን መስጠታቸው ጠንካራ የሀገር ፍቅርና እርካታ እንዲኖራቸው በማድረግ በሙያ በሚሰሩበት አጋጣሚም የስራ ልምድ የሚያገኙበት እንደሚሆንም ተመላክቷል።
በሀብታሙ ተክለስላሴ
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision