ዓለምአቀፋዊ ዜና

ኢጋድ በምስራቅ አፍሪካ ተጨባጭ የኢኮኖሚ ትሥሥር ዕውን ለማድረግ ይሠራል-ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ

By Alemayehu Geremew

February 15, 2022

አዲስ አበባ፣ የካቲት 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) በቀጠናው ተጨባጭ የኢኮኖሚ ትሥሥር ዕውን ለማድረግ እንደሚሠራ የድርጅቱ ዋና ጸሃፊ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ተናገሩ።

ዋና ጸሃፊው በብራስልስ በተካሄደው የአፍሪካ ቀንድ የሚኒስትሮች ኢኒሼቲቭ ስብሰባ ላይ ተካፍለዋል፡፡

በስብሰባውም ዶክተር ወርቅነህ፥ የኢኒሼቲቩን አራት ምሰሶዎች ማለትም ቀጠናዊ የመሠረተ-ልማት ትሥሥር፣ የተሳለጠ የንግድ ከባቢ፣ ለውጫዊ ተጽዕኖ ምላሽ የመስጠት ችሎታ እንዲሁም የቀጠናውን ሀገራት ኢኮኖሚ ለማሳደግ የሰው ኃብት የማበልፀግ አስፈላጊነት ላይ ማብራሪያ መስጠታቸውን የኢጋድ ሥራ አስፈጻሚ ጽህፈት ቤት ቃል አቀባይ ኑር ሞሐሙድ ሼክ ጠቁመዋል፡፡

በእነዚህ ምሰሶዎች ላይ መሥራትም ቀጠናዊ ተጽዕኖን ለመቋቋም እንደሚያግዝ ዶክተር ወርቅነህ ማስገንዘባቸውንም ሥራ አስፈጻሚው በትዊተር ገፃቸው በኩል አስታውቀዋል።