በጋምቤላ ክልል በአውሮፓ ኅብረት የገንዘብ ድጋፍ የሚተገበር የእናቶች እና ሕጻናት ጤና ማሻሻያ መረሃ-ግብር ተጀመረ
አዲስ አበባ፣የካቲት 9፣2014 (ኤፍ ቢሲ) በጋምቤላ ክልል በአውሮፓ ኅብረት የገንዘብ ድጋፍ የሚተገበር የእናቶች እና ሕጻናት ጤና ማሻሻያ መረሃ-ግብር በይፋ ተጀምሯል።
“ለሥርዓተ-ፆታ እኩልነት የማኅበራዊ ጤና ቁርጠኝነት” በሚል መረሃ-ግብር በክልሉ ባሉ አራት ወረዳዎች ላይ ፕሮጀክቱ እንደሚተገበር ተገልጿል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በመድረኩ ላይ ተገኝተው እንደተናገሩት፥ የማኅበረሰብ ጤና አገልግሎት ተጠቃሚነት አሁን ካለበት ደረጃ ለማሻሻል የሚመለከታቸው መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የጤናን አጀንዳ የጋራ በማድረግ እየሠሩ እንጀሚገኙ ገልጸዋል።
የእናቶችንና ሕጻናት ሕመምና ሞት ለመቀነስ ከቤት እስከ ትምህርት ቤት በየዕድሜያቸው የሚያስፈልጋቸውን የአመጋገብ ሥርዓት እንዲከተሉ በማስተማርና ክትትል በማድረግ የአዕምሮና የአካል ጥንካሬ ብቃት ያለው ቀጣይ የሀገር ተስፋ ሰጪ ትውልድ ለማፍራት ሁሉም የድርሻውን ሊያበረክት ይገባል ብለዋል።
የፕሮጀክቱ አስተባባሪ የሆኑት ዶ/ር ኡጁሉ ኡጁሉ እንደገለፁት፥ ለሦስት ዓመት ከ268 ሚሊየን ብር በላይ በጀት ተይዞ በሥረዓተ-ምግብ ላይ እየተሠራ አንደሆነ እና በቀጣይም ሁሉንም የጤና ዘርፎች ለማሻሻል እየተሠራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
በክልሉ ውስጥ ለፕሮጀክቱ ትግበራ ከተለዩ ወረዳዎች፥ ዲማ ፣ መንገሺ፣ ኢታንግ እና መኮይ የተጠቀሱ ሲሆን በአካባቢዎቹም 20 ትምህርት ቤቶች ፣ 12 ጤና ጣቢያዎች፣ ሦስት የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች ተለይተዋል፡፡
ወረዳዎቹ የተመረጡት ችግሩ ጎልቶ ስለሚታይባቸው መሆኑንም መገለፁን ከጋምቤላ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ያገኘነዉ መረጃ ያመላክታል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!