Fana: At a Speed of Life!

ድርቁ በዱር እንስሳት ላይ እያስከተለ ያለውን ጉዳት ለመቀነስ ጥረቶች እየተደረጉ ነው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ድርቁ በዱር እንስሳት ላይ እያስከተለ ያለውን ጉዳት ለመቀነስ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን የቦረና ብሔራዊ ፓርክ ገልጿል።

በዚህም ገንዳ በመስራት ውሃ በተሽከርካሪ የማቅረብ ሙከራዎች በመደረግ ላይ ቢሆኑም ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በፓርኩ በነበረው ቅኝት በድርቁ የሞቱ የዱር እንስሳትን ተመልክቷል።

የፓርኩ የስካውቶች ሀላፊ ኦኮቱ ዲዳ፥ ድርቁን ተከትሎ የዱር እንስሳት ለሞትና የተለያዩ ችግሮች መዳረጋቸውን አንስተዋል።

በተለይም በፓርኩ የሚገኙ ቨርቺልና ግሬቪ የተባሉ የሜዳ አህያ ዝርያዎች እየሞቱ መሆኑን ነው ያስረዱት።

በፓርኩ ከ27 አመት በላይ ያገለገሉት ኦኮቱ ዳዲ÷ ከዚህ ቀደም መሰል ችግሮች ተከስተው የነበረ ቢሆንም የአሁኑ ግን ያስከተለው ጉዳት ይበልጣል ብለዋል።

በቦረና ብሔራዊ ፓርክ ከ20 የሚበልጡ የእንስሳት ዝርያዎች የሚገኙ ሲሆኑ፥ ከእነዚህ ውስጥ ድርቅ የመቋቋም አቅማቸው ዝቅተኛ የሆኑት ከርከሮ፣ የሜዳ አህያና አጋዘን በውሃና መኖ ችግር እየሞቱ ነው።

የፓርኩ ስካውት ሀላፊ ችግሩን ለመፍታት መኖና ውሃ ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም በፓርኩ የተለያዩ አካባቢዎች የውሃ ገንዳዎች ተገንብተው በቦቴዎች እየተሞሉ አገልግሎት እየሰጡ ሲሆን ÷ ሳርም ለማቅረብ ሙከራ እየተደረገ ነው ተብሏል።

የፓርኩ ስካውቶች ለችግሩ ትኩረት በመስጠት ለመፍታት የተቀናጁ ስራዎች እንዲሰሩ ጠይቀዋል።

በአፈወርቅ እያዩና ታሪኩ ለገሰ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.