ለአንድ ሣምንት ምርቱን አቋርጦ የነበረው የፊንጫ ስኳር ፋብሪካ ዳግም ስራ ጀመረ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በነዳጅ አቅርቦት ችግር ለአንድ ሣምንት ማምረት አቋርጦ የነበረው የፊንጫ ስኳር ፋብሪካ ዳግም ምርት መጀመሩን የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ገለጸ፡፡
በዓመት 2 ነጥብ 7 ሚሊየን ኩንታል ስኳርና 20 ሚሊየን ሊትር ኢታኖል የማምረት አቅም ያለው የፊንጫ ስኳር ፋብሪካ÷ በነዳጅ እጥረት ምክንያት ለአንድ ሣምንት ማምረት አቁሞ እንደነበር ተገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን እንዳስታወቀው÷ ነዳጅ ጫኝ መኪና አሽከርካሪዎች ለደኅንነታቸው በመስጋት ወደ አካባቢው ለመሄድ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ከየካቲት 2 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ለአንድ ሣምንት ማምረት አቁሞ ነበር፡፡
ሆኖም ከየካቲት 7 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ የነዳጅ አቅርቦት ችግሩ በመስተካከሉ ወደ መደበኛ የማምረት ስራው መመለሱን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በአካባቢው የሸኔ ታጣቂ በመግባት በፋብሪካው ላይ ጉዳት አድርሷል የሚለው መረጃ አሉቧልታ መሆኑን ያመለከተው የስኳር ኮርፖሬሽን÷ ከየካቲት 8 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ወደ መደበኛ የማምረት ስራ ገብቷል።
በኢትዮጵያ ከ1991 ዓ.ም ጀምሮ ስኳር ማምረት የጀመረው የፊንጫ ስኳር ፋብሪካ እስከ 2003 ዓ.ም ድረስ ብቸኛው የኢታኖል አምራች ሆኖ የቆየም ግዙፍ ፋብሪካ ሲሆን÷ በ1991 ዓ.ም ስኳር ማምረት ሲጀምር የነበረው 6 ሺህ 476 ሄክታር መሬት አሁን ላይ 21 ሺህ ሄክታር መድረሱ ታውቋል።