Fana: At a Speed of Life!

አቶ ሙሰጠፌ መሀመድ በ155 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነባውን የሀርተሼክ-ሀርሺን የጠጠር መንገድ አገልግሎት አስጀመሩ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሶማሌ ክልል ርዕሰ መሰተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሀመድ የሚመራ የክልሉ ከፍተኛ አመራር ቡድን ደረጃውን በጠበቀ መልኩ በ155 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነባውን የሀርተሼክ-ሀርሺን የጠጠር መንገድ አስመርቆ ለአገልግሎት ክፍት እንዲሆን አስደረገ።

በሶማሌ ክልል መስኖና ተፋሰስ ልማት ቢሮ የተገነባው የሀርተሼክ-ሀርሽን ጠጠር መንገድ ፕሮጀክት በተያዘለት በጀትና የጊዜ ገደብ የተጠናቀቀ ሲሆን፥ በክልሉን ሦስት ዞኖች የሚገኘውን ህዝብ የሚያስተሳስር መሆኑ ተገልጿል።

የመንገዱ ግንባታ ሁለት ዓመት የፈጀና 50 ኪ.ሜ የሚሸፍን መንገድ መሆኑንም በምረቃ ሥነሥርዓቱ ላይ የተገኙት የመሰኖና ተፋሰስ ልማት ቢሮ የስራ ሃላፊዎቹ ገልጸዋል።

አቶ ሙስጠፌ መሃመድ ዑመር በምረቃ ስነስርዓት ላይ እንደተናገሩት ፥ የክልሉ መንግሥት በክልሉ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የተከሰተዉን የተፈጥሮ የድርቅ አደጋ ከመቋቋም ጎን ለጎን የህብረተሰቡን የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች ለመመለስ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ዛሬ የተመረቀው የሀርተሼክ-ሀርሽን ደረጃዉን የጠበቀ የጠጠር መንገድ በመሰራቱ ለሁለቱ ወረዳዎችና ለአካባቢዉ ህብረተሰብ ትልቅ ፋይዳ የሚሰጥ ከመሆኑ ባሻገር ፥ ከዚህ በፊት በአካባቢው የመንገድ መሰረተ ልማት ባለመኖሩ ምክንያት እናቶች በወሊድ ወቅት ከፍተኛ ችግር ይደርስባቸው የነበሩት በርካታ ችግሮችን የሚቀርፍ መሆኑን ገልጸዋል።

የሶማሌ ክልል መሰኖና ተፋሰስ ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ መሀመድ ፋታህ ፥ ከዚህ በፊት በአካባቢዉ መንገድ ባለመኖሩ ምክንያት የአካባቢው ማህበረሰብ ለተለያዩ ችግሮች ሲጋለጥ እንደነበር በመግለፅ ፥ የተመረቀው መንገድ የበርካታ ዓመታት ጥያቄ መልስ የመለሰ እንደሆነ ተናግረዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ አክለውም ፥ በሁለቱ ወረዳዎች የሚኖረው ህብረተሰብ የመንገድ መሰረተ ልማት ችግር በዘላቂነት ከመፍታቱ ባሻገር መንገዱ በፋፋን፣ጃራርና ዶሎ ዞኖችን የሚገኙ ህብረተሰብን ያስተሳስራል ማለታቸውን ከክልሉ ምግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.