በአፋር ከልል የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ክትባት ተጀመረ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፋር ክልል ሁለተኛው ዙር የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ክትባት በክልል ደረጃ መሰጠት ተጀመረ።
በዘመቻ የሚሰጠው ክትባት ማስጀመሪያ ሥነ-ሥርዓት ላይ የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ኑሩ መሀመድ እንዳሉት፥ በክልሉ ካለፈው ዓመት አጋማሽ ጀምሮ የኮሮና ቫይረስ ክትባቱ በተለያዩ ጤና ተቋማት ሲሰጥ ቆይቷል።
ዛሬ በክልል ደረጃ ሁለተኛው ዙር ክትባት መጀመሩንና ህብረተሰቡም እንዲከተብ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መከናወናቸውን ነው ሃላፊው የተናገሩት።
አሸባሪው ህወሓት በክልሉ በጤና ተቋማት ላይ ባደረሰው ውድመትና በተወሰኑ የክልሉ አካባቢዎች ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት ሁለተኛው ዙር ክትባት በአውሲ ረሱ እና በገቢ-ረሱ ዞኖች ስር ባሉ የጤና ተቋማት እንደሚሰጥም አስታውቀዋል።
በሁለቱ ዞኖች ከዛሬ ጀምሮ ለአስር ቀናት በሚሰጠው ክትባት ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ ለሆኑ 43 ሺህ 218 ሰዎች ተደራሽ ለማድረግ መታቀዱን ገልጸዋል።
በቀሪዎቹ ዞኖች ምቹ ሁኔታ መኖሩ ታይቶ ክትባቱ የሚሰጥ መሆኑን ነው የጠቆሙት።
በግንዛቤ እጥረት ምክንያት ቀደም ሲል በክልሉ የሚፈለገውን ያህል ሰው የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚያግዘውን ክትባት እንዳልወሰዱ አቶ ኑሩ አውስተዋል።
ይህን ለማስተካከል ከሀገር ሽማግሌዎቾ፣ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከሴቶችና የወጣት አደረጃጀቶች እንዲሁም ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተደጋጋሚ ውይይት በማድረግ ብዥታዎችን የማጥራት ሥራ መከናወኑን ተናግረዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!