Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ እና እስራኤል ቁርኝት ዘመናትን ያስቆጠረና ታሪካዊ ነው-በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር

አዲስ አበባ፣ የካቲት 10 ፣ 2014 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር ከሆኑት አቶ አለልኝ አድማሱ ጋር ተወያይተዋል።
ሁለቱ ሃገራት የሚያስተሳስሯቸው በርከታ ጉዳዮች መኖራቸውን የተናገሩት ሚኒስትሩ፥ ግንኙነታቸውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በትኩረት እንደሚሰራም ጠቁመዋል፡፡
አቶ መላኩ በቅርቡ ኢትዮጵያ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የደረሰባትን ተጽዕኖ ለመቀልበስ በተደረገው የ “በቃ” ዘመቻ ላይ በርካታ እስራኤላዊያን ተሳታፊ መሆናቸውን አንስተው፥ይህም የሁለቱን ሃገራት ህዝቦች ትስስር በይበልጥ ያጎላ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ለዚህም ላሳዩት አጋርነት ለእስራኤል ህዝብ ያላቸውን ልዩ አክብሮት ገልጸዋል፡፡
አያይዘውም ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ በርካታ የእስራኤል ባለሃብቶች መዋዕለ ንዋያቸውን በማፍሰስ ላይ እንዳሉና በተሰማሩባቸው የስራ መስኮችም ውጤታማ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት የውጪ ባለሃብቶች በሃገሪቱ ኢንቨስት እንዲያደርጉ በርካታ ምቹ ሁኔታዎችን ማመቻቸቱን የገለጹት ሚኒስትሩ፥ ከእነዚህም አንዱ የተቀናጀ አግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
መንግስት ካስገነባቸው 4 ፓርኮች ውስጥ 3ቱ ስራ መጀመራቸውን የተናገሩት ሚኒስትሩ፥ በዚህ ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት ላላቸው ባለሃብቶች ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ቃል ገብተዋል፡፡
በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር የሆኑት አቶ አለልኝ አድማሱ የኢትዮጵያ እና እስራኤል ቁርኝት ዘመናትን ያስቆጠረና ታሪካዊ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
በርካታ እስራኤላዊያን በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ ጽኑ ፍላጎት ቢኖራቸውም በኢትዮጵያ መንግስት በኩል በተለይም ከጉምሩክ በኩል የሚስተዋለው ቢሮክራሲ መሻሻል እንዳለበትና የኢትዮጵያ መንግስትም ለዚህ ጉዳይ ልዩ ትኩረት መስጠት እንደሚገባውም አምባሳደሩ መግለጻቸውን ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.