Fana: At a Speed of Life!

በኢፋድ ድጋፍ የሚካሄዱ የልማት ስራዎች የህብረተሰቡን ህይወት ለማሻሻል ከፍተኛ ሚና አላቸው – አቶ ርስቱ ይርዳ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 10 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በተባበሩት መንግስታት የግብርና ልማት ዓለም አቀፍ ፈንድ (ኢፋድ) ፕሮግራም የሚካሄዱ የልማት ስራዎች የህብረተሰቡን ህይወት ለማሻሻል ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው አቶ ርስቱ ይርዳ ገለጹ።

የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳ ከግብርና ልማት ዓለም አቀፍ ፈንድ (ኢፋድ) ዳይሬክተር ከማዊራ ቺትማ ጋር በጽ/ቤታቸው ተወያይተዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ በኢፋድ ፕሮግራም የሚካሄዱ የልማት ስራዎች የህብረተሰቡን ህይወት በማሻሻል ረገድ ሚናቸው ከፍተኛ መሆኑንም አብራርተዋል።

በዝናብ ላይ የተመሰረተውን የአርሶና አርብቶ አደሩን ህይወት ለማሻሻል አነስተኛ መስኖዎችን መገንባት የላቀ ውጤት እያመጣ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በቀጣይም ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ከፍ ለማድረግ ከአጋር ድርጅቶች ጋር የሚደረገውን የትብብር ስራ እናጠናክራለን ብለዋል።

በዚህም የመስኖ ልማት ስራውን ውጤታማ ለማድረግ የክልሉ መንግስት 1 ቢሊየን ብር የሚጠጋ በመመደብ እየተሰራ መሆኑንም ርዕሰ መስተዳድሩ በውይይታቸው ጠቁመዋል።

የውሃ አማራጭ በሌለባቸው አካባቢዎች ከዝናብ የሚገኘውን ውሃ በማጠራቀም እና ለመስኖ የማዋል ሰራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

በቆላማ አካባቢዎች ተደጋጋሚ የጎርፍ አደጋ እና ተያያዥ ችግሮች በአርብቶ አደሩ ህይወት ላይ ያስከተለው ጉዳት ከፍተኛ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ በትብብር መስራት እንደሚያስፈልግም አስረድተዋል።

የግብርና ልማት ዓለም አቀፍ ፈንድ (ኢፋድ) ዳይሬክተር ማዊራ ቺትማ እንደገለጹት ÷በክልሉ እየታየ ያለው ሰላምና ጸጥታ አስተማማኝ ደረጃ ላይ መድረሱን በአድናቆት መመልከታቸውን ተናግረዋል።

በተለይ አነስተኛ መስኖ ልማት የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን ያለውን ፋይዳ በመግለጽ በአርሶና አርብቶ አደሩ ህይወት ላይ ለውጥ ማምጣቱንም ዳይሬክተሯ በአብነት ጠቅሰዋል።

የህብረተሰቡን ህይወት ለመቀየር በሚካሔዱ የልማት ስራዎች ላይ በትብብር ለመስራት መዘጋጀታቸውንም መናገራቸውን ከክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.