የኤች አር 6600 የውሳኔ ሀሳብ እንዳይጸድቅ በዳያስፖራ አባላት የተጀመረው ጥረት ቀጥሏል
አዲስ አበባ፣ የካቲት 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሜሪካ ምክር ቤት የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ኢትዮጵያን በተመለከተ የተዘጋጀው ኤች አር 6600 የውሳኔ ሀሳብ እንዳይጸድቅ በኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የተጀመረው ጥረት መቀጠሉ ተገለፀ።
ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢትዮጵያ አሜሪካ የዜጎች ምክር ቤት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አምሳሉ ካሳው እንደተናገሩት ፥ ሂደቱን ለመቃወም እስካሁን ለ790 የአሜሪካ የምክር ቤት አባላት እና ባልደረቦቻቸው ባለ አስር ነጥብ የተቃውሞ ደብዳቤ በእጃቸው እንዲደርሳቸው ተደርጓል።
ሰነዱ ለአንድ ወገን ያደላ መሆኑን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ፥ አኘባሪው ህወሓት እድሜያቸው ያልደረሱ ህጻናትን በጦርነት ማሰለፉን፣በአማራና አፋር ክልሎች የፈጸማቸውን የዘር ጭፍጨፋዎች፣ የንብረት ውድመት እና አያሌ ለጆሮ የሚከብዱ ግፎችንም እንዲሁ እንደዋዛ አልፏቸዋል ነው ያሉት።
በአሜሪካ የዴንቨር ኮሎራዶ ነዋሪ እና የማህበራዊ ፍትህ ተሟጋች ነብዩ አስፋው በበኩላቸው፥ ለኢትዮጵያ በጎ በማያስቡ የኮንግረስ አባላት የተረቀቀው የውሳኔ ሀሳብ ኢትዮጵያን በኢኮኖሚ ከማድቀቅ እስከ መንግስት ለውጥ የሚሰፋ ድብቅ ሴራን ይዟል ነው ያሉት።
በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ስለሀገራቸው ምንም እንዳይሉ፣ ከአሜሪካ መንግስት ተቃርነው እንዳይቆሙ፣ የንግድ እና ገንዘብ እንቅስቃሴን በመገደብ ዜጎች ለከፋ ድህነት እንዲዳረጉ፣ ለጋሽ ሀገራት ኢትዮጵያን እንዳይረዱ፥ ከረዱ ግን ማዕቀብ እንደሚጣልባቸው ጭምር የሚያስፈራራ ረቂቅ መሆኑን አንስተዋል።
በጥቅሉ ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ የኢትዮጵያ መንግስት ለሀገር ሰላም እና መረጋጋት እየወሰደ ያለውን እርምጃ በመካድ የተዘጋጀው ይህ የውሳኔ ሀሳብ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት የበለጠ የሚያሻክር በመሆኑ ለአሜሪካ መንግስትም አይጠቅምም ብለዋል።
የሽብርተኛው ህወሓት ደጋፊ በሆኑ የአሜሪካ ኮንግረስ አባላት የተረቀቀውንና የኤች አር 6600 የተሰኘውን ይህን የውሳኔ ሀሳብ ውድቅ ለማድረግ የተጀመረውን ጠንካራ እንቅስቃሴ ሁሉም ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች እንዲቀላቀሉትም ጠይቀዋል።
በአፈወርቅ ዓለሙ
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!