Fana: At a Speed of Life!

የፌዴራል የሥራ ቋንቋ እንዲሆኑ የተመረጡ ቋንቋዎች አገልግሎት እንዲጀምሩ ዝግጅት እየተደረገ ነው

 

አዲስ አበባ፣ የካቲት 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የቋንቋ ልማት ፖሊሲ የፌዴራል የሥራ ቋንቋ እንዲሆኑ የተመረጡ ቋንቋዎች ወደ ሥራ እንዲገቡ ለማስቻል ዝግጅት እየተጠናቀቀ መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

ከአማርኛ በተጨማሪ የፌዴራል የስራ ቋንቋ እንዲሆኑ በኢትዮጵያ የቋንቋ ፖሊሲ የተቀመጡትን ቋንቋዎች ወደ ሥራ ለማስገባት በተዘጋጁ ሰነዶች ላይ በባለድርሻ አካላት ዛሬ በአዳማ ተመክሮበታል።

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጄላ መርዳሳ በወቅቱ እንደገለጹት÷ በፖሊሲው እውቅና ያገኙ ቋንቋዎችን ወደ ስራ ለማስገባት የትርጉምና አስተርጓሚነትን ጨምሮ ሌሎች ደንቦችን ለማዘጋጀት የተለያዩ ጥናቶች ተካሂደዋል።

ቋንቋዎቹን ወደ ስራ ለማስገባትና የፌደራል የስራ ቋንቋ ለማድረግ ብዙ ሂደት ስለሚያስፈልግ ቅድመ ዝግጅቶቹን ለማጠናቀቅ አስፈላጊ ስራዎችን እያከናወንን ነው ብለዋል።

የሚኒስቴሩ የባህልና ቋንቋ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ወርቅነሽ ብሩ በበኩላቸው÷ ከአማርኛ በተጨማሪ የፌዴራል የሥራ ቋንቋ እንዲሆኑ በኢትዮጵያ የቋንቋ ልማት ፖሊሲ የተቀመጡትን አራቱን ቋንቋዎች ወደ ስራ ለማስገባት እየሰራን ነው ያሉ ሲሆን÷  በዚህም ኦሮምኛ፣ ሱማሊኛና አፋርኛ ቋንቋዎች ፖሊሲውን የመተርጎም ስራዎች መጠናቀቃቸውን አስታውቀዋል።

አሁን የቀረን የትግረኛ ቋንቋ ፖሊሲ ነው፤ እሱንም መፍትሄ እየፈለግን ነው ብለዋል።

ትርጉማቸው የተጠናቀቀው ወደ ክልሎቹ ተልከው በየደረጃው ያለው ህብረተሰብ እንዲወያይበትና በትክክል እንዲገነዘበው እየተሰራ መሆኑን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ከአማርኛ በተጨማሪ የፌዴራል የሥራ ቋንቋ እንዲሆኑ የተመረጡት ቋንቋዎች አፋን ኦሮሞ ፣ ትግርኛ፣ ሶማልኛና አፋርኛ መሆናቸው ይታወቃል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.