Fana: At a Speed of Life!

62 ሰዎችን አሳፍሮ ወደ ደሴ ይጓዝ የነበረ የህዝብ ማመላለሻ አውቶብስ የእሳት ቃጠሎ አደጋ አጋጠመው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 11፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ከአዲስ አበባ ወደ ደሴ 62 ሰዎችን አሳፍሮ ይጓዝ የነበረ አንድ ሀገር አቋራጭ የህዝብ ማመላለሻ አውቶብስ የእሳት ቃጠሎ አደጋ እንዳጋጠመው በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን የጅሌ ጥሙጋ ወረዳ ፖሊስ ፅህፈት ቤት አስታወቀ።

የእሳት ቃጠሎው የንብረት ውድመት ቢያደርስም በሰው ህይወት ላይ ምንም አይነት ጉዳት አለመድረሱ ተገልጿል።

አውቶብሱ አደጋው ዛሬ ረፋድ ላይ ያጋጠመው በዞኑ ጅሌ ጥሙጋ ወረዳ ጎዳ ቀበሌ ሲደርስ መሆኑን በጽህፈት ቤቱ የመንገድ ደህንነትና ትራፊክ ክፍል ባለሙያ ዋና ሳጅን ወንድወሰን ጌታሁን ተናግረዋል፡፡

በደረሰው አደጋ ወሎ ዩኒቨርሲቲ ለመመዝገብ ተሳፍረው ይጓዙ የነበሩ ተማሪዎችን ሻንጣና ዶክመንት ጨምሮ የሌሎችን ተሳፋሪዎች ንብረትም ሙሉ በሙሉ ከአውቶቡሱ ጋር መውደሙንም ገልጸዋል።

አውቶብሱ የእሳት ቃጠሎ አደጋ ያጋጠመው በሞተሩ ላይ በተከሰተ የቴክኒክ ችግር እንደሚሆን ጠቅሰው ፥ የቃጠሎው መንስዔ ለማጣራት ሙሉ የምርመራ ስራ መጀመሩን አስረድተዋል።

ተሽከርካሪው ከሽዋ ሮቢት ጀምሮ የጭስ ምልክት ያሳይ እንደነበርና አሽከርካሪው ‘‘ፍሬን ሸራ ነው’’ በሚል ሲያሽከረክር እንደነበር ከተሳፋሪዎች መረጃ መገኘቱንም አመልክተው ፥ አሽከርካሪውና ረዳቱ በቁጥጥር ስር ውለው የማጣራት ስራ እየተካሄደ መሆኑም ታውቋል።

በተሽከርካሪው ውስጥ የነበሩ ተሳፋሪዎችም በሌላ መኪና ወደ ደሴ መላካቸውን አመልክተዋል፡፡

አሽከርካሪዎች የተሽከርካሪውን አካል በመፈተሽ የተሳፋሪውን ደህንነት የመጠበቅ ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸውም ማስገንዘባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.