ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ጫና እየጨመረ ነው – ዶክተር ሊያ ታደሰ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ጫና እየጨመረ መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለጹ፡፡
ሚኒስትሯ የጅማ ዩኒቨርሲቲ የካንሰር ህክምና ማዕከልን በይፋ ያስመረቁ ሲሆን፥ በሀገሪቱ የተላላፊ በሽታዎችን የስርጭት መጠን መቀነስ ቢቻልም ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ ጫናቸው እየጨመረ ይገኛል ብለዋል፡፡
ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች መካካል አንዱ የካንስር ህመም መሆኑን የገለፁት ዶክተር ሊያ፥ በየዓመቱ ከ70 ሺህ በላይ ሰዎች በካንሰር እንደሚያዙ ተናግረዋል፡፡
ከ70 ሺዎችም የህክምና አገልግሎት የሚያገኙት ከ15 በመቶ እንደማይበልጡ እና በሦስት የህክምና አማራጮች የካንሰር ህክምና እየተሰጠ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡
አንደኛው ኬሞቴራፒ ወይም መድሃኒት ሲሆን፥ አሁን ላይ 17 ሆስፒታሎች አገልግሎቱን እየሰጡ እንደሚገኙ፣ ሌሎቹ የቀዶ ህክምና እና የጨረር ህክምና መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ብቻ ሲሰጥ የነበረው የካንሰር የጨረር ህክምና አገልግሎት አሁን በጅማ ዩኒቨርሲቲም መጀመሩ ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል፡፡
በቀጣይ የጨረር ህክምና ማዕከላትን ብዛት ወደ ሰባት ከፍ ለማድረግ በትኩረት ይሰራልም ነው ያሉት፡፡
በሀገራችን የጡትና የማህፀን በር ጫፍ ካንስር ለብዙ ሴቶች ህልፈተ ህይወት ምክንያት ነው ያሉት የሀይለማሪያምና ሮማን ፋውንዴሽን መስራች ወይዘሮ ሮማን ተስፋዬ በበኩላቸው፥ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ የማህፀን በር ጫፍ ቅደመ ካንሰር ልየታ ምርመራና ህክምና የሚሰጡ ማዕካላት ቁጥር 17 ብቻ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
አሁን ላይ ከ1 ሺህ መብለጣቸው ይበል የሚያሠኝ ተግባር ነው ብለዋል፡፡ በቀጣይም ፋውንዴሽኑ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመሆኑ በጋራ እንደሚስራም አረጋግጠዋል፡፡
መንግስት የካንስር በሽታን ለመከላከል ማህበረስብ አቀፍ የመከላከል ስራን ተግባራዊ ማድረግ፣ የተለያዩ የክትባት አገልግሎቶችን መስጠት፣ የቅድመ- ልየታ ስራ እና የህክምና አሰጣጥ ስርዓቱን ማዘመንን አቅጣጫ አስቀምጦ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል ያሉት ደግሞ የጤና ሚኒስትር ድኤታ ዶክተር ደረጃ ዱጉማ ናቸው፡፡
በተመስገን አለባቸው
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!