ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሕዳሴ ግድብን የኃይል ማመንጨት ሥራ አስጀመሩ
ግድቡ ሐምሌ 2012 ዓ ም ላይ 4 ነጥብ 5 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሃን በመጀመሪያ ዙር የያዘ ሲሆን፥ ባለፈው ነሐሴ ወር 2013 ላይ ደግሞ 13 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሃን መያዝ ችሏል።
ግድቡ ካሉት 13 ተርባይኖች ዩኒት መካከል በግድቡ ዩኒት አሥር ላይ የሚገኘው አንዱ ተርባይን ከተሳካ ተከላ እና ሙከራ በኋላ ዛሬ ኃይል ማመንጨት ጀምሯል።
ዛሬ ወደ ሥራ የገባው ይህ ተርባይን 375 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም አለው።
ዛሬ እየተከናወነ ባለው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኃይል ማመንጨት ማብሰሪያ ሥነ-ሥርዓት ላይ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሥፍራው ተገኝተው የግድብን የኃይል ማመንጨት ሥራ በይፋ አስጀምረዋል፡፡
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ጅማሬው ላይ በ80 ቢሊየን ብር ወጪ ይገነባል የሚል እቅድ የነበረ ቢሆንም፥ እስካሁን ድረስ ከ163 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ ተደርጎበታል።
የሕዳሴ ግድብ 145 ሜትር ከፍታ ያለው ሲሆን፥ ወደጎን 1 ሺህ 780 ሜትር ርዝመት ይኖረዋል።
ግድቡ የሚይዘውን 74 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሃ ሙሉ በሙሉ ሲይዝም ውሃው የሚተኛበት ሥፍራ ርዝመት 246 ኪሎ ሜትር ይደርሳል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ