ዛሬ ለኢትዮጵያ የብርሀን መባቻ ነውና መላው ኢትዮጵያውያን እንኳን ደስ አለን-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ
አዲስ አበባ የካቲት 13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ዛሬ ለኢትዮጵያ የብርሀን መባቻ ነውና መላው ኢትዮጵያውያን እንኳን ደስ አለን ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መልዕክት አስተላለፉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ዛሬ የአፍሪካ ትልቁ የኃይል ማመንጫ የህዳሴ ግድብ ሥራ መጀመሩን በማስመልከት ባስተላለፉት መልዕክት÷ ይህ ለአኅጉራችን እንዲሁም አብረናቸው ሠርተን በጋራ ለመጠቀም ለምንሻ የታችኛው ተፋሰስ አገራት የምሥራች ነው ብለዋል።
ዐባይ ወንዛችን ሀገራችንን አልምቶ ጎረቤቶቻችንን ሊያረሰርስ ጉዞውን መቀጠሉን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ዛሬ ለኢትዮጵያ የብርሀን መባቻ ነውና መላው ኢትዮጵያውያን እንኳን ደስ አለን ሲሉ የብስራት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለህዳሴው ግድብ ከጥንስሱ እስከ ስኬቱ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የሀገር መሪዎች እና ለተለያዩ ባለሙያዎች ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በዚህም መሰረት አጼ ኃይለሥላሴ በዚያን ጊዜ ፕሮጀክቱን መፈጸም ባይችሉ እንኳን ቀጣዩ ትውልድ ይገነባዋል ብለው በማመን የፕጀክቱን ሀሳብ እና ዲዛይን በመቅረጻቸው እጅግ ምስጋና ይጋባቸዋል ነው ያሉት፡፡
ከንጉሡ በኋላም የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስቴር አቶ መለስ ዜናዊ ጊዜው አሁን ነው ብለው ፕሮጀክቱን በማስጀመራቸው ምስጋና እንደሚገባቸው ገልጸዋል፡፡
አቶ ኃይለ ማርያም ደሣለኝም ፕሮጀክቱን በማስቀጠል የራሳቸውን ገንቢ አስተዋጽኦ በማድረጋቸው ሶስቱም አመራሮች የጀመሩት ፕሮጀክት ስለሆነ እኛ ለውጤት ያበቃነው ማመስገን ግድ ይለናል ብለዋል፡፡
በተመሳሳይ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ቦርድ አመራርሮችን፣ ባለሙያዎች፣ የህዳሴ ግድብ ሰራተኞች፣ የመከላከያና የፀጥታ ሃይሎችን እንዲሁም መላው ኢትዮጵያውያንን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን አመሰግናለሁ ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ።
በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ምስጋና ካቀረቡላቸው ሌሎች አመራሮችና አካላት መካከል አቶ አለማየሁ ተገኑ፣ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ፣ ዶክተር ምህረት ደበበ፣ ኢንጂነር ስመኘው በቀለ፣ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ፣ ዶክተር አብርሃም በላይ፣ ኢንጂነር አዜብ አስናቀ፣ አቶ ግርማ ብሩ እና የፐብሊክ ዲፕሎማሲ አባላት ይገኙበታል፡፡
በተለይም ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ስኬት የዕውቀት እና የገንዝብ ድጋፍ ላበረከተው የኢትዮጵያ ህዝብ ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በተያያዘም በአሉባልታ እንደተባለው ኢትዮጵያ የተፋሰሱ ሀገራትን ዜጎች ውኃእንዳይደርሳቸው በማድረግ የምታስርብ አለመሆኗን ዛሬ በተግባር አሳይታለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ይህም የጋራ ስኬት በመሆኑ እንኳን ደስአላችሁ ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ማንንም የመጉዳት ዓላማ እንደሌላት ገልጸው÷ ዋናው ግቧ እስካሁን በሃይል አቅርቦት እጦት የተነሳ እየተሰቃዩ ያሉ የህብረተሰባችንን ክፍሎች ችግር መቅረፍ እና ከድህነት መውጣት መሆኑን በተለይ የተፋሰሱ ሃገሮች ሊገነዘቡ ይገባል ነው ያሉት፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ