Fana: At a Speed of Life!

ኮምቦልቻን ከአሸባሪው ህወሓት ወረራ ነፃ በማውጣት ሂደት ለተሳተፉ አካላት ዕውቅና ተሰጠ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 14፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኮምቦልቻ ከተማንና ነዋሪዎቿን ከአሸባሪው እና ወራሪው የህወሓት ቡድን ነፃ በማውጣት ሂደት ለተሳተፉ አካላት ምስጋና እና እውቅና ተሰጠ።
የኮምቦልቻ ከተማ ማህበረሰብ እና የከተማ አስተዳደሩ ባዘጋጁት በዚሁ ስነስርዓት ላይ ወራሪውን እና አሸባሪውን የህወሓት ቡድን ለመከላከል በህልውና ዘመቻው ወቅት ትልቅ ድርሻ ለተወጡ የሀገር መከላከያ ሰራዊት አመራሮችና አባላት፣ የአማራ የፀጥታ ሀይሎችና የፌደራል ፖሊስ አባላት በዚሁ መርሃ ግብር እውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡
የኮምቦልቻ ከተማ ምክትል አስተዳዳሪ ኢንጂነር አህመድ የሱፍ በስነ ስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ “ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲዖል ድረስ እገባለሁ” ያለው አሸባሪው ህወሓት በርካታ ዘረፋዎችን ፈፅሟል ፤ “የኢትዮጵያን አንድነት ለማላላት ያስችለኛል” ያለውን ትርክት ሁሉ ፈጥሯል ብለዋ፡፡
ይሁን እንጅ የኢትዮጵያ ዘብ የሆኑ የመከላከያ ሰራዊት አባላት የአማራ ልዩ ኃይል፣ የፌደራል ፖሊስ አባላትና ሌሎች የጸጥታ አካላት የሀገርን ክብር በማስመለስ የተቃጣባትን ጥቃት መመከት መቻላቸውንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
ኢንጂነር አህመድ አክለውም÷“የሰራችሁትን ያህል ምስጋናችን ትልቅ ባይሆንም እንኳን እናመሰግናችኋለን” ነው ያሉት።
በዕለቱ የክብር እንግዳ የሆኑት የአማራ ክልል ብልፅግና አደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሞላ፥ “ጊዜው ዓባይ ከመፍሰስ ቆሞ ለኢትዮጵያ ብርሃን መሆን የጀመረበት ስለሆነ ልዩ ስሜት አለው”፥ ዛሬ እዚህ ለመገኘታችንም በርካታ ጀግኖች በተለያዩ ግንባሮች ደማቸው አፍስሰዋል ብለዋል።
“ኢትዮጵያ ጠላቶቿን ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን ጀግኖቿንም ታወድሳለች፤ ስለዚህም የመከላከያ ሰራዊት የአማራ ልዩ ኃይል ፣ ፋኖና ሚሊሻ አወድሰናቸውም አመስግነናቸውም አንጠግብም” ሲሉ ተናግረዋል።
በፕሮግራሙ ላይ የክልሉ አፈ ጉባዔ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ፣ የመከላከያ ሚኒስትር ዴዔታ ዶክተር አህመዲን አህመድ ፣ የደቡብ እዝ አዛዥ ሌተናል ጄነራል ሰለሞን ኢተፋን ጨምሮ የተለያዩ የክልል ከፍተኛ ባለስልጣናት ተገኝተዋል።
ለመከላከያ ሚኒስቴር ዋንጫና የምስክር ወረቀት የተሰጠ ሲሆን፥ ለኢ.ፌ.ዲ.ሪ መከላከያ ሰራዊት ማእከላዊ ዕዝ ፣ የምዕራብ እዝ ፣ ምስራቅ እዝ ፣ ደቡብ እዝ፣ 6ኛ እዝ ፣ ለኮማንዶ ልዩ ዘመቻ፣ ለአየር ኃይል፣ ለኢትዮጵያ የፌደራል ፖሊስ፣ ለአማራ ልዩ ኃይል ፣ አማራ ፖሊስ፣ ለአማራ ሚሊሻ ፣ ለአማራ አድማ ብተና እና ለአማራ ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን የምስጋና እንዲሁም የእውቅና የምስክር ወረቀት ተሰጥቷል ።
በተጨማሪም በእውቅና እና የምስጋና መርሃ ግብሩ ላይ ለፋኖ ቤተሰቦች እውቅና የተሰጠ ሲሆን ፥ ለተለያዩ አመራሮችና ወታደራዊ መኮንኖችም የጋቢ ማልበስ ስነስርዓት ተካሂዷል ።

በፀጋየ ወንድወሰን

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.