Fana: At a Speed of Life!

በሬዲዮ ፋና ለ19 ዓመታት ለተላለፈው አባ ጃምቦ ድራማ እውቅና ተሰጠ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 14፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሬዲዮ ፋና ላለፉት 19 ዓመታት ሳይቆራረጥ በአፋን ኦሮሞ ለተላለፈው አባ ጃምቦ ተከታታይ የሬዲዮ ድራማ እውቅና ተሰጠ።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት 25ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን በማክበር ላይ የሚገኝ ሲሆን፥ በዛሬው እለትም የዚሁ አካል የሆነው የአባ ጃምቦ ተከታታይ የሬዲዮ ድራማ እውቅና የመስጠት ስነ ስርዓት ተካሂዷል።

በመድረኩ ላይም የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው፣ የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ከበደ ዴሲሳ እና የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ በቀለ ሙለታን ጨምሮ ሌሎች የስራ ኃላፊዎች እና የኪነ ጥበብ ቤተሰቦች ተገኝተዋል።

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው፥ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት 25ኛ ዓመት የምስረታ በዓል እንኳን አደረሳችሁ፤ ፋና በሬዲዮ ታሪክ የሚታወቅ እና ጠንካራ ከሆኑ መገናኛ ብዙሃን አንዱ ነው ብለዋል።

ዶክተር ሂሩት፥ ፋና በሬዲዮ የብዙ ቤተሰቦችን ቤት ዳሷል፤ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካ ዘርፍም የተለያዩ ጉዳዮችን በማቅረብ ማህበረሱን አስተምሯልም ነው ያሉት።

መገናኛ ብዙሃን ያለ ኪነጥበብ ባዶ ነው ያሉ ሲሆን፥ ለዚህ በማሳያነትም አባ ጃምቦ ተከታታይ የሬዲዮ ድራማን አንስተዋል።

በበርካቶች ዘንድ ተወዳጅ ሆኖ የቆየው አባ ጃምቦ ድራማም ለዚህ በመብቃቱ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን፥ አባ ጃምቦ ድራማ ላለፉት 19 ዓመታት ሳይቆራረጥ በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ በርካታ ጉዳዮችን ሲያሰርፅ የቆየ ነው ብለዋል።

አባ ጃምቦ ድራማ በሁሉም ኢትዮጵያውያን ቤት የነበረ ድራማ ነው፤ አባ ጃምቦ ለኦሮሞ ማህበረሰብ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ህዝቦችንም ቋንቋ ሲያስተምር የቆየ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ድራማው ሳይቆራረጥ ለዚህ እንዲበቃ ላደረጉ ተዋናዮች፣ የድራማው ቤተሰቦች እና ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንኳን ደስ አላችሁም ብለዋል።

የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ በቀለ ሙለታ በበኩላቸው፥ ፋና 25 ዓመታትን ተጉዟል፤ በእነዚህ ዓመታት በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚ እና በፖለቲካ ዘርፍ በርካታ ስራዎችን ሲሰራ ቆይቷል ብለዋል።

ፋና ባለፉት 25 ዓመታት በርካታ ዝግጅቶች ነበሩት፤ ከእነዚህ ውስጥ ለ19 ዓመታት በተከታታይ ህዝቡ ዘንድ ሲደርስ የነበረው አባ ጃምቦ የሬዲዮ ድራማ አንዱ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

አባ ጃምቦ የሬዲዮ ድራማ በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ ተወዳጅ ነበር ያሉት አቶ በቀለ፥ በኢትዮጵያ ሬዲዮ ታሪክም በተከታታይ ድራማ ለረጅም ዓመታት በመተላለፍ የመጀመሪያው ነው የሚል እምነት አለኝ ብለዋል።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት 25ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ምክንያት በማድረግ ለአባ ጃምቦ ድራማ እውቅና መስጠቱን የገለፁት አቶ በቀለ፥ በቀጣይም በሌሎች ቋንቋዎች ሲተላለፉ ለነበሩ ዝግጅቶች እውቅና የመስጠት ስነ ስርዓት ይካሄዳል ብለዋል።

በመድረኩ ላይ የኦሮሞ ኪነ ጥበብ ጉዙ ከየት ወዴት በሚል ርእስ ጥናታዊ ፅሁፍ የቀረበ ሲሆን፥ አባ ጃምቦ ድራማ በዚህ ላይ ምን ሚና አለው በሚልም ውይይት ተደርጎበታል።
በድራማው ላይ ለተሳተፉ ተዋናዮችም የተለያዩ የእውቅና የምስከር ወረቀቶች እና ከ50 ሺህ እስከ 100 ሺህ ብር ተሸልመዋል።

ከ19 ዓመት በኋላ አባ ጃምቦ በዚህ መልኩ እውቅና እንዲሰጠው ላስቻሉት የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አክሲዮን ማህበር ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ በቀለ ሙለታም ተዋንያኑ የኦሮሞን ባህላዊ ልብስን ሸልመዋል።

አባ ጃምቦ ድራማ በደራሲ እና ጋዜጠኛ ሰብስቤ አበበ እየተደረሰ ላለፉት 19 ዓመታት በየሳምንቱ አርብ ምሽት ከ3 ሰዓት ከ30 በኋላ ለ30 ደቂቃ በሬዲዮ ፋና ሲተላለፍ መቆየቱ ይታወሳል።

የድራማው ይዘትም ፖለቲካ፣ ተምህርት፣ ኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ፣ ታሪክ፣ ባህል እና የህዝብ እሴት ላይ መሰረት በማድረግ ሲተላለፍ የቆየ ነው።

በሙለታ መንገሻ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.