በጦርነት ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸውን ከተሞች መልሶ ለማቋቋም 58 ከተሞች የጥምረት ስምምነት ተፈራረሙ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 14፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በጦርነት የወደሙና ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸውን ከተሞች መልሶ ለማቋቋም 58 ከተሞች የጥምረት ስምምነት መፈራረማቸውን የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ገለጸ።
ጉዳት የደረሰባቸውን ከተሞች መልሶ የመገባንት ሂደት በተፋጠነ መልኩ ለማስኬድ የሚያግዝ አሰራር መዘርጋቱንም አስታውቋል።
ሚኒስቴሩ የበጀት ዓመቱን የመጀመሪያ ስድስት ወራት የስራ አፈጻጸም በሀዋሳ ከተማ እየገመገመ ሲሆን÷ በቤቶች ግንባታ፣ በመሬት አቅርቦትና የግንባታውን ዘርፍ በማዘመን፣ ከተሞችን ለነዋሪዎች የተሻለና ምቹ በማድረግ የአሰራር ማዕቀፍ መዘርጋቱ ተገልጿል።
በአማራና አፋር ክልሎች ለከፍተኛ ጉዳት የተዳረጉ ከተሞች ነዋሪዎች የዕለት ድጋፍ እንዲያገኙ ለማስቻል ሚኒስቴሩ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ፋንታ ደጄን አስታውሰዋል።
በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው ከተሞች በአፋጣኝ መልሶ ለመገንባትና ከነበረው የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማስቻል ከተሞች የሚረዳዱበት የትስስር ስርዓት መመቻቸቱን አስታውቀዋል።
በዚህም ዛሬ 58 ከተሞች የጥምረት ስምምነት መፈራረማቸውን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው÷ አዲስ አበባን ጨምሮ በሁሉም የክልል ከተሞች የቤት ፍላጎትና እጥረት ችግር ማቃለል እንዲቻል የግል አልሚዎች የሚሳተፉበት አሰራር መዘርጋቱንም ጠቅሰዋል።
የመንግስት ሰራተኞችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች በማህበር እየተደራጁ የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ የሚያገኙበት አሰራር በተጠናከረ መልኩ ለማስቀጠል ጥረት እየተደረገም ነው ብለዋል።
በከተሞች እየታየ ያለውን ህገወጥነትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለማቃለል ከተለመደው አሰራር ወጣ ያለ ጣልቃገብነት ያለበት የቁጥጥር አሰራር መጀመሩንም ኢዜአ ዘግቧል።
አዳዲስ ከተሞች በያሉበት በመቆርቆር ወደ ትልልቅ ከተሞች የሚደረጉ ፍልሰቶችን ለመከላከል የሚያስችል ስራ መጀመሩን አመላክተዋል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!