Fana: At a Speed of Life!

በእሳት አደጋ የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ ሦስት ሕፃናት ሕይወት አለፈ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 15፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በስልጤ ዞን ሚቶ ወረዳ ድንገት በተከሰተ የእሳት ቃጠሎ አደጋ የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ የሦስት ሕጻናት ህይወት ማለፉን ፖሊስ አስታወቀ።

አደጋው የደረሰው በወረዳው “ግርንዝላ ሸፎዴ” የገጠር ቀበሌ ትናንት ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ተኩል አካባቢ መሆኑን የሚቶ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ረዳት ኢንስፔክተር አክመል ከይረዲን ገልጸዋል።

በዚህም በመኖሪያ ቤት ውስጥ የነበሩ የስድስት፣ የአምስት እና የአንድ ዓመት ዕድሜ ያላቸው የአንድ ቤተሰብ አባል የሆኑ ሦስት ህፃናት ሕይወታቸው ማለፉን አስታውቀው፥ ከሟቾቹ መካከል ሁለቱ ሴቶች እንደሆኑ አመልክተዋል።

የእሳት አደጋው ሁለት መኖሪያ ቤቶችን ሙሉ በሙሉ ሲያወድም በቤት ውስጥ የነበሩ አምስት የቤት እንስሳትንና ሌሎች ንብረቶችን ማውደሙንም ኢንስፔክተር አክመል ተናግረዋል።

በተጨማሪ በግቢ ውስጥ የነበረና ለጊዜው ግምቱ ያልታወቀ የበቆሎ፣ ገብስ እና የጥራጥሬ እህል ማውደሙን አመልክተዋል።

“የአካባቢው ህብረተሰብ የእሳት ቃጠሎው ለማጥፋት ባደረገው ርብርብ ወደሌሎች ቤቶች እንዳይዛመትና ተጨማሪ አደጋ እንዳያደርስ ለማድረግ ተችሏል” ብለዋል።

የወረዳው የሥራ ሃላፊዎችና የአካባቢው ማህበረሰብ ችግሩ የገጠማቸውን የቤተሰብ አባላት ቦታው ድረስ በመሄድ እያጽናኑ መሆኑንም ተናግረዋል።

ፖሊስ በአሁኑ ወቅት የአደጋውን መንስኤ እያጣራ መሆኑን የገለጹት አዛዡ ፥ ወቅቱ ደረቃማና ከፍተኛ ነፋስ የሚስተዋልበት በመሆኑ ህብረተሰቡ ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ ከመሰል አደጋዎች ራሱንና ሌሎችንም መጠበቅ እንዳለበት ማሳሰባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.