Fana: At a Speed of Life!

የደቡብ ክልል በጦርነት ለወደሙ የጤና ተቋማት ከ9 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 15፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ክልል ጤና ቢሮ በደቡብ ወሎ ዞን በጦርነቱ ለወደሙና ለተዘረፉ የጤና ተቋማት ከዘጠኝ ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የመድኃኒትና የህክምና መሳሪያ ድጋፍ አደረገ።

ድጋፉን የደቡብ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ እንደሻው ሽብሩ ለደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አብዱ ሁሴን አስርክበዋል።

ድጋፉን የተረከቡት የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አብዱ ሁሴን እንዳሉት ፥ በጦርነቱ የወደሙ ጤና ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም የተለያዩ ጥረቶች በመደረግ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የተደረገው ድጋፍ በዋናነት የድንገተኛና የእናቶችን የወሊድ አገልግሎቶች በተሟላ መንገድ ለመስጠት የሚረዳ መሆኑን ገልፀው ፥ የክልሉ ጤና ቢሮ በጦርነቱ ለወደሙ ተቋማት እያደረገ ስላለው ድጋፍ አመስግነዋል።

የደቡብ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ እንደሻው ሽብሩ ፥ ድጋፉ ቅድመ ዳሰሳውን ማዕከል ባደረገ መልኩ በዋናነት በጦርነቱ ለወደሙ የጤና ተቋማት የሚጠቀሙባቸው የህክምና ግብዓቶችን ያካተተ መሆኑን ገልጸዋል።

አጠቃላይ ግምቱ ከ9 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት መድኃኒትና የህክምና መሳሪያ፣ ኮምፒውተርና ፕሪንተር መሆኑን ገልጸው ፥ በዞኑ የጤና አገልግሎት ለመስጠት የሚያግዝ ነው ብለዋል።

ከአሁን በፊትም ከ2 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጣ መድኃኒትና የህክምና መሳሪያ ድጋፍ መደረጉን ያስታወሱት አቶ እንደሻው ፥ የደቡብ ክልል የጦርነቱ ሰለባ የሆኑ 7 ሆስፒታሎችን በቋሚነት በመደገፍ ላይ መሆናቸውን ገልጸው፥ ድጋፋም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው የተናገሩት።

በዞኑ 101 ጤና ጣቢያ፣ ሰባት ሆስፒታሎችና 398 ጤና ኬላዎች የጦርነቱ ሰለባ መሆናቸውን የደቡብ ወሎ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ጌታቸው በለጠ ተናግረዋል። ለተደረገላቸው ድጋፍም ምስጋና ማቅረባቸውን ከዞኑ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.