የብሄራዊ በጎ ፈቃድ የማህበረሰብ አገልግሎት ማብሰሪያ ፕሮግራም ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 15፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የብሄራዊ በጎ ፈቃድ የማህበረሰብ አገልግሎት ማብሰሪያ ፕሮግራምተካሄደ።
በፕሮግራሙ ላይ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድን ጨምሮ የክልሎች ርዕሳነ መስተዳደሮች እና የከተማ አስተዳደሮች ከንቲባዎች ተገኝተዋል፡፡
በመርሃ ግብሩ የሚሳተፉ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተውጣጡ የዩኒቨርሲቲ እና የቴክኒክና ሙያ ምሩቃንም በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ እየተካሄደ ባለው የማብሰሪያ ስነ ስርአት ላይ ተገኝተዋል፡፡
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በዚህም ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት በጎ ፈቃድ ማለት አንድ ሰው የራስን ጊዜና ሀብት ሰውቶ ሌላ ወንድም እና እህቱን ሲያግዝ መሆኑን አስረድተዋል።
ወጣቱቹ ለዚህ ተግባር ተነሳስተው ሀገርን አስቀድመው በዚህ ደረጃ ሰውን ለማገልገል በመነሳታቸው እድለኛ ናቸው ብለዋል።
“የምትፈፅሙት መልካም መቼ እና እንዴት እንደሚከፈላችሁ ባላውቅም የሆነ ጊዜ ግን ክፍያውን የምታገኙበት ኢንቨስትመንት ነው” ብለዋል ወጣቶቹን።
በወጣቱ ውስጥ ያለውን እውቀት እና ማዕድን አውጥቶ ለመልካም ነገር መጠቀም እንደሚገባም ነው የተናገሩት።
ወጣቶች በመርሀ ግብሩ በሙሉ ልባቸው እንዲሳተፋ እና የሚያገኟቸውን ክህሎቶች ለሕይወታቸው መሠረታዊ አድርገው እንዲቆጥሯቸውም መክረዋል።
ወጣቶች ኃይላቸውን ለፍሬያማ ጉዳዮች እንዲጠቀሙ፣ ተግባራቶቻቸውን በጥበብ እንዲከውኑ፣ ጊዜያቸውን በጥንቃቄ በጥቅም ላይ እንዲያውሉ፣ ትኩረታቸውንም ሙሉ ለሙሉ በአዎንታዊ ጉዳዮች ላይ ብቻ እንዲያደርጉም አሳስበዋል።
በመርሃ ግብሩ ኢትዮጵያ አገራቸውን የሚወዱና የአገልጋይነት ስሜት የተላበሱ ወጣቶችን ለማፍራት ያለመ ነው።
ለአገልግሎቱ አምስት የበጎ ፈቃድ አምባሳደሮች ተመርጠዋል፤ ከመላ አገሪቷ የተውጣጡ ከ116 ሺህ በላይ ወጣቶችም ተመዝግበዋል።
የሠላም ሚኒስቴር ሰሞኑን በሰጠው መግለጫ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ የሚሰጠው መንግስታዊ ካልሆኑ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጋር በመተባበር እንደሆነ ገልጿል።
መርሃ ግብሩ የዜጎችን አብሮ የመኖር እሴት ያዳብራል ተብሎ እንደሚጠበቅም ነው ሚኒስቴሩ ያስታወቀው፡፡
በመርሃ ግብሩ ለመሳተፍ ከ116 ሺህ በላይ ወጣቶች የተመዘገቡ ሲሆን፡ ዛሬ በማብሰሪያ ስነ ስርአቱ ላይ እየተሳተፉ የሚገኙት 10 ሺህ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በመጀመሪያው ዙር ለሁለት ወራት ይሰለጥናሉ ተብሏል፡፡
ወጣቶቹ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመስጠታቸው ከሚያገኙት እርካታ በተጨማሪ በተለያዩ ተቋማት መቀጠር የሚያስችላቸው የስራ ልምድ ይሰጣቸዋልም ነው ያለው የሰላም ሚኒስቴር፡፡
በጎ ፈቃደኞቹ ወደ ተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል ከመመደባቸው በፊት በክህሎት፣ ስብዕና እና አካላዊ ግንባታ ላይ የሚያተኩሩ ስልጠናዎችን ይወስዳሉ፡፡
በፋሲካው ታደሰ