Fana: At a Speed of Life!

“የፍቅር ጥያቄዬን አልተቀበልሽኝም” በሚል አሲድ ደፍቶ ጉዳት ያደረሰው ግለሰብ በ14 ዓመት በጽኑ እስራት ተቀጣ

አዲስ አበበ፣ የካቲት 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) “የፍቅር ጥያቄዬን አልተቀበልሽኝም” በሚል አሲድ በመድፋት በአንዲት ሴት ላይ ጉዳት ያደረሰ ግለሰብ በ14 ዓመት ጽኑ እስራት መቀጣቱን በምስራቅ ጎጃም ዞን የሁለት እጁ እነሴ ወረዳ ፍርድ ቤት አስታወቀ።

የፍርድ ቤቱ ሰብሳቢ ዳኛ አቶ አማረ አያሌው እንደገለጹት÷ ግለሰቡ በተመሰረተበት ክስ በሰነድና የሰው ማስረጃ ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ የፍርድ ውሳኔ ተላልፎበታል።

ተበዳይ የጤና ባለሙያ ስትሆን በሁለት እጁ ነሴ ወረዳ ቀራንዮ በተባለች አነስተኛ የገጠር ከተማ በአንድ ግለሰብ መድኃኒት ቤት ተቀጥራ ትሰራ ነበር።

ተከሳሹ ግለሰብ “ያቀረብኩልሽን የፍቅር ጥያቄዬ አልተቀበልሽኝም” በሚል በቀል ተነሳስቶ ታህሳስ 18 ቀን 2014 ዓ.ም ከቀኑ 11 ሰዓት አካባቢ ከሥራ ስትመለስ መንገድ ላይ ጠብቆ አሲዱን በፊቷና በራሷ ላይ ይደፋባታል።

ግለሰቡ ድርጊቱን ከፈፀመ በኋላ ከአካባቢው ተሰውሮ ከአንድ ወር በላይ እንደጠፋ ይቆያል። ፖሊስ ባደረገው ክትትል ጥር 26 ቀን 2014 ዓ.ም በሞጣ ከተማ በአንድ ግለሰብ ቤት ተደብቆ ያገኘዋል።

ግለሰቡ ወንጀሉን ለመፈፀም ያነሳሳው ለተበዳይዋ ያቀረብኩት የፍቅር ጥያቄ ተቀባይነት አላገኘም በሚል ተነሳስቶ እንደሆነም ለፍርድ ቤቱ በቀረበ ማስረጃ ተረጋግጧል ብለዋል ዳኛው።

ግለሰቧ ሰውነቷ ላይ በተደፋው አሲድ በፊቷ፣ በግማሽ እራሷና በአንድ ጡቷ ላይ ከፍተኛ አካላዊ ጉዳት እንደደረሰባት በማስረጃ መረጋገጡንም ነው ሰብሰቢ ዳኛው የተናገሩት።

የወረዳው ፍርድ ቤት ትናንት ባዋለው ችሎት ተከሳሹ ግለሰብ በ14 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ መወሰኑን ዳኛው መግለጻቸውን የኢዜአ ዘገባ ያመላክታል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.