የ2013 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤት ይፋ ሆነ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በተለያዩ አገራዊ ምክንያቶች ተራዝሞ የቆየው የ2013 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤት ይፋ መደረጉን አገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ አስታወቀ።
ፈተናውን ለመውሰድ ከተመዘገቡ 617 ሺህ 991 ተማሪዎች ውስጥ 96 በመቶ የሚሆኑት ፈተናውን በሁለት ዙር መውሰዳቸው ተመላክቷል፡፡
በአጠቃላይ ፈተናውን ከወሰዱት ውስጥ 277 ሺህ ያህሉ ሴቶች መሆናቸው ነው የተገለጸው ፡፡
የፈተና እርማቱ ደኅንነታቸው አስተማማኝ በሆኑና ከንክኪ ነፃ በሆኑ የማረሚያ ማሽኖች አስፈላጊው የደኅንነት ጥበቃ ተደርጎ በጥንቃቄ መከናወኑም ተብራርቷል፡፡
የፈተናዎች ውጤት በትምህርት ዓይነት፣ በትምህርት ቤትና በተማሪ ደረጃ ሰፊ የውጤት ትንተና በማካሄድ የእያንዳንዱ የትምህርት ዓይነት ውጤት መገምገሙምንም ኤጀንሲው ጠቁሟል፡፡
ከሲቪክስ የትምህርት ዓይነት በስተቀር በሌሎቹ የትምህርት ዓይነቶች የተገኘው የውጤት ትንተና ሲታይ ምንም ዓይነት ችግር የሌለበት በመሆኑ እንዲመዘገብ ተደርጓል ።
በተናጠል የፈተና ደንብ ጥሰት የፈጸሙ 141 ተማሪዎች ላይ ከውጤት መሰረዝ ጀምሮ የተለያየ አስተዳደራዊ እርምጃ እንደተወሰድም ተመላክቷል፡፡
ለከፍተኛ ትምህርት ገብተው ለመማር ብቁ የሚሆኑ ሁሉም ተማሪዎች ለመግቢያነት የሚያገለግሉ የትምህርት ዓይነቶችን አጠቃላይ አማካይ ነጥብ 50 በመቶ እና በላይ ያመጡ ተማሪዎች ይሆናሉ ተብሏል፡፡
ለምሳሌ በሰባት የትምህርት ዓይነት ተፈትነው ከ600 ለሚያዝላቸው ተማሪዎች አማካይ ውጤት 300 እና በላይ ማምጣት ይጠበቅባቸዋል።
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ገብተው ለሚማሩ ተማሪዎች፥ የዩኒቨርሲቲዎችን የመቀበል አቅም በማገናዘብ ዝርዝር የመግቢያ ነጥብ ወደፊት የሚገለጽ ይሆናል ተብሏል።
ስለሆነም ተማሪዎች የሚከተሉትን አማራጮች በመጠቀም ውጤታቸውን ማወቅ እንደሚችሉ ተገልጿል።
1) በትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ዌብሳይት፡- http://result.neaea.gov.et
2) በትምህርት ሚኒስቴር ዌብሳይት፡- http://result.ethernet.edu.et
3) በቴሌግራም ቦት (Telegram Bot):- @moestudentbot – በዚህ ማስፈንጠሪያ በመግባትና Exam Result የሚለውን በመጫን በመልክት መጻፊያው ላይ የመለያ ቁጥራቸውን በማስገባት እና የ ምልክት በመጫን መላክና ውጤታቸው ማየት ይችላሉ።
4) በ9444 የ ኤስ ኤም ኤስ (9444 SMS) ፡- በመልክት ማስተላለፊያ መጻፊያ ላይ የመለያ ቁጥራቸውን በማስገባት ወደ 9444 በመላክ ውጤታቸውን ማየት ይችላሉ።
አዎንታዊ ድጋፍ ለሚሹ አመልካቾች፡- http://student.ethernet.edu.et በመግባት ማመልከት ይችላሉ። በተመሳሳይ በውጤት ላይ ቅሬታ ያላቸው ተማሪዎችም http://result.neaea.gov.et በመግባት እና Compliant የሚለውን በመጫን ቅሬታቸውን በፎርሙ ላይ በመሙላት ማቅረብ ይችላሉ ተብሏል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!