Fana: At a Speed of Life!

ኮሚሽኑ ሥራውን በገለልተኝነት በመሥራት አገራዊ ኃላፊነቱን መወጣት አለበት – አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ

አዲስ አበበ፣ የካቲት 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ሥራውን በገለልተኝነት በመሥራት የተሰጠውን ህዝባዊ ኃላፊነት ሊወጣ እንደሚገባ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ አሳሰቡ፡፡

የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን የስራ መጀመሪያ ትውውቅ መርሀ ግብር ዛሬ ተካሂዷል፡፡

አፈ ጉባኤ ታገሰ በዚህ ወቅት ባሰሙት ንግግር፥ ፖለቲካ ከአገር በላይ ስላልሆነ ኮሚሽኑ በማቋቋሚያ አዋጁ መሰረት የተሰጠውን ኃላፊነት ገለልተኛ በመሆን ታሪካዊ ሥራ ሰርቶ ማለፍ እንደሚገባው አስገንዝበዋል፡፡

በአገራዊ ምክክሩ የሚሳተፉት የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ አንድ አካል መሆናቸውን ጠቁመው÷ የምክክሩ ባለቤት ህዝቡ ስለሆነ ትክክለኛ ውሳኔ የሚጠበቀው ከህዝቡም እንደሆነ ነው አፈጉባኤው የተናገሩት፡፡

ኮሚሽኑ እቅድ አውጥቶ ወደ ሥራ እንዲገባ አስፈላጊው የሰው ኃይል፣ ቢሮ እና ግብኣቶች ሊሟሉለት ስለሚገባ ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር አስፈለጊው በጀት እንደሚመደብም ጠቁመዋል፡፡

የኮሚሽኑ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መስፍን አርኣያ በበኩላቸው÷ የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን አባል ሆነው እንዲሰሩ ኃላፊነት የሰጣቸው ሕዝቡ በመሆኑ ሙሉ ጊዜያቸውን ሰጥተው በኃላፊነት መንፈስ ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን እና ከሚዲያውና ከሌሎች አካላት ጋር በጋራ እንደሚሰሩ ነው የተናገሩት፡፡

አያይዘውም የአስፈፃሚው አካል ወይም የመንግሥት ጣልቃ-ገብነት እንደማይኖር እምነታቸው መሆኑን ጠቁመው በኮሚሽኑ አሠራር ውስጥ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት የሚኖር ከሆነ ግን ኃላፊነታቸውን በፈቃዳቸው እንደሚለቁ ማሳሰባቸውን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.