የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያና ፓኪስታን የጋራ የንግድ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ተስማሙ

By Alemayehu Geremew

February 23, 2022

አዲስ አበባ፣ የካቲት 16፣ 2014 (ኤፍ ቢሲ) ኢትዮጵያና ፓኪስታን የጋራ የንግድ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር መስማማታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ከፓኪስታን የኢንቨስትመንት ቦርድ፣ከፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት፣ከኢስላማባድ ንግድ ምክር ቤት፣ ከፓኪስታን ኩባንያ ዋና ስራ አስፈፃሚዎች እንዲሁም ከስትራቴጂክ ጥናት ተቋም ተወካዮች ጋር ተወያይተዋል።

በወይይታቸውም የሀገሪቱ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የሆነው ኢስላማባድ ከኢትዮጵያውያን ጋር የንግድ ሥራዎችን ለመሥራት እና ከኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጋር በትብብር ለመስራት ያላቸውን ፍላጎት አሳይተዋል።

የንግድ ምክር ቤቱ የፓኪስታን ነጋዴዎች ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ቪዛ እንዲሰጡ የጠየቀ ሲሆን÷ ከኢትዮጵያ የንግድ ማህበረሰብ ጋር በመሆን የተለያዩ ምርቶችን ወደ አገር ውስጥ በማስገባትና ወደ ውጭ በመላክ እንዲሁም በጋራ ጉዳዮች ላይ ለመስራት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው ገልጿል።

አምባሳደር ሬድዋን በበኩላቸው÷ የፓኪስታን ነጋዴዎች ኢትዮጵያ ሲደርሱ ቪዛ እንደሚመቻችላቸው እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ፓኪስታኗ ካራቺ ከተማ በረራ ለማድረግ በዝግጅት ላይ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

በኢትዮጵያ በግብርና፣ ፋርማሲዩቲካል፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ አግሮ ፕሮሰሲንግ፣ ጨርቃ ጨርቅና ቆዳ ዘርፎች ላይ የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዳሉ መጠቆማቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።