በኢትዮጵያ የተከሰተው ድርቅ የዓለም አየር ንብረት ለውጥ ሰላባ መሆናችንን ማሳያ ነው -ኤጀንሲው
አዲስ አበባ፣ የካቲት 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የተከሰተው ድርቅ ሀገሪቱ የአለም የአየር ንብረት ለውጥ ሰላባ ለመሆኗ ማሳያ መሆኑን የብሔራዊ ሚቲዮሮሎጂ ኤጀንሲ አስታውቋል።
ኤጀንሲው የአየር ትንበያና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ዳይሬክተር ጫሊ ደበሌ፥ በኢትዮጵያ በተለይም በደቡብ ሶማሌ፣ በቦረና፣ በጉጂ እና ባሌ ቆላማ አካባቢዎች የተፈጠረው ድርቅ ከፓስፊክ ውቅያኖስ የላይኛው አካል የሚነሳው ”ላሊና” ተብሎ የሚጠራው አየር ከመደበኛ በላይ መቀዝቀዝ ያስከተለው የዝናብ እጥረት መሆኑን ገልጸዋል።
ይህንን ጨምሮ የአየር ንብረት ለውጦችን እና በዚያ ሳቢያ የሚከሰቱ የተፈጥሮ አደጋዎችን የሚተነብየው ብሔራዊ የሚቲዮሮሎጂ ኤጀንሲ ትንበያ ቢያደርግም ትንበያው የአጫጭር እንጂ የረጅም ወቅቶች አይደሉም ብለዋል ዳይሬክተሯ።
በዚህም ረጅም የትንበያ ጊዜ ከ2 እስከ 7 ዓመት ሲሆን፥ ይህም በዓለም ትልልቅ የውሃ አካላት ጸባይ እና በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የሚወሰን መሆኑን ጠቁመዋል።
አሁን የ”ላሊና” ወቅት እያበቃ ነው ያሉት ዳይሬክተሯ፥ ድርቁ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ከሁለት ወራት ገደማ በኋላ የዝናብ ዕድል እንደሚኖር ትንበያዎች ማመላከታቸውን ጠቁመዋል።
ይሁን እንጂ ድርቁ በዘነበ ማግስት ብቻ የሚቆም ባለመሆኑ በውሃ አያያዝና አጠቃቀም እንዲሁም በዘላቂ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ስራ ላይ ማተኮር እንደሚገባ ኤጀንሲው ጠቁሟል።
በሶዶ ለማ
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!