ከተማ አስተዳደሩ በሶማሌ ክልል ለተከሰተው ድርቅ 22 መኪና የመኖ ድጋፍ አደረገ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 17፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሶማሌ ክልል ለተከሰተው ድርቅ 22 መኪና የመኖ ድጋፍ አደረገ።
የከተማ አስተዳደሩ ለሶማሌ ክልል ያደረገው የመኖ ድጋፍ በሁለተኛ ዙር የተደረገ ሲሆን ፥ ከልደታ ክፍለ ከተማ ነዋሪዎችና አስተዳደር የተዋጣ መሆኑ ተገልጿል።
ድጋፉን ያስረከቡት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ፥ ችግሩ የሶማሌ ክልል ብቻ አለመሆኑን ለማሳየት ከጎናችሁ አብረን ነን ብለዋል።
ከንቲባዋ አክለውም ክልሉ ለሰው ልጅ ቅድሚያ በመስጠቱ በሰው ህይወት ላይ አደጋ አለመድረሱን ገልፀው ፥ ችግሩ እስኪቀረፍም ከጎናችሁ ነን ሲሉ ተናግረዋል።
የመኖ ድጋፉን የተረከቡት የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድ አቶ ሙስጠፌ መሃመድ ፥ የከተማ አስተዳደሩ ላበረከተው ድጋፍ አመስግነው ፥ አሁን የተከሰተው ድርቅ ላለፉት አርባ ዓመታት ያልታየ ነው ብለዋል።
ድርቁ ከመከሰቱ በፊት የክልሉ ካቢኔ ችግሩ እንደሚከሰት በመገንዘቡ ባደረገው ጥረት በሰው ህይወት ላይ አደጋ እንዳያደርስ ማድረግ መቻሉንም ጨምረው መግለፃቸውን ከከንቲባ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።