በጠ/ሚ ዐቢይ የተመራው ልዑክ ከአውሮፓ ህብረት ባለስልጣናት ጋር ፍሬያማ ውይይት አካሂዷል-አምባሳደር ዲና ሙፍቲ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 17፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ለ6ኛው የአውሮፓና አፍሪካ ህብረቶች የጋራ ጉባኤ ወደ ቤልጂየም ብራሰልስ አቅንቶ የነበረው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተመራው ልዑክ ከህብረቱ ባለስልጣናት ጋር ፍሬያማ የሁለትዮሽ ውይይቶች ማካሄዱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፥ በጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አሕመድ የተመራው ልዑክ በብራሰልስ ቆይታው ከአውሮፓ ህብረት ባለስልጣናት ጋር ፍሬያማ የሁለትዮሽ ውይይቶች ማካሄዱን ተናግረዋል፡፡
በተመሳሳይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የተመራ ቡድን በሙኒክ ቆይታው 58ኛው የጸጥታ መድረክ ላይ መሳተፉን አንስተዋል፡፡
በዚህም ከስዊዲን፣ አየር ላንድ እና ጀመርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር በእውቀት ሽግግር፣ ሰላምና ደህንነት እንዲሁም በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ መክሯል ነው ያሉት፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ ኢትዮጵያ ሰላምን ለማረጋገጥ እያደረገች ያለውን ጥረት እንደሚያደንቁና ድጋፋቸውን እንደማያቋርጡ መግለጻቸውም ተጠቁሟል።
አምባሳደር ዲና የቀይ ባህርና የአፍሪካ ቀንድ አገራት የሚጋሯቸው ችግሮች ስላሏቸው በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው በውይይቱ መነሳቱን አመልክተዋል።
በአፍሪካ ቀንድ የአሚሶም ተልዕኮ በአፍሪካ ቀንድ ሽብርን ለመከላከል የጎላ ጠቀሜታ አለው መባሉን የገለጹት ቃል አቀባዩ፥ በቀይ ባህር ፎረም ላይ ኢትዮጵያ መገለል የለባትም የሚል መልክት መተላለፉንም ጠቁመዋል፡፡
ህገ ወጥ ስደት እና ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዘውውርን በጋራ መታገል እንደሚገባም አጽንኦት ተሰጥቶበታል ነው ያሉት።
የአፍሪካ ቀንድ አገራትን ለማስተሳሰር ኢትዮጵያ የአንበሳውን ድርሻ ለመጫወት የሚያስችል ብቃት እንዳላት መጠቆሙንም ገልጸዋል፡፡
አቶ ደመቀ ከሙኒክ የፀጥታ መድረክ ጎን ለጎን በተካሄደው የጣና ፎረም በመሳተፍ በአፍሪካ ቀንድ ስላለው የአሸባሪነት፣ የህገ ወጥ ሰዎች ዝውውር፣ የህገ ወጥ ጦር መሳሪያዎች እንቅስቃሴ የዘር ግጭት እና የውጭ ጣልቃ ገብነት የቀጠናው ችግር እንደሆኑ ማብራሪያ መስጠታቸውም በመግለጫው ተነስቷል፡፡
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ህውሃት በንጹሃን ላይ የፈፀመውን አረመኔያዊ ድርጊት ማውገዙ እንደ ጥሩ እርምጃ የሚወሰድ እንደሆነ ጠቅስዋል።
ወደ ትግራይ ያልተገደበ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ይኑር ሲል ያነሳውን ሃሳብ ኢትዮጵያ በተግባር እየፈጸመቸው ያለ ጉዳይ መሆኑንም ነው ያብራሩት።
ለሰላም ቦታ ለመስጠትም ሃገራዊ የምክክር መድረክ ለማካሄድ ዝግጅቷን እያጠናቀቀች እንደምትገኝ አንስተዋል።
በሳዑዲ ካሉ ዜጎች ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያውያንን ወደ ሃገራቸው ለመመለስ የሚያስችሉ ቅድመ ሁኔታዎች በመካሄድ ላይ ናቸው።
ግብጽ ከግድቡ ጋር ተያይዞ የምታነሳቸው ገዳዮች እንዲሁም የህግና የቴክኒክ ጉዳዮች በሂደት እልባት እያገኙ መሆኑን አምባሳደር ዲና ተናግረዋል።
በሱዳን የተፈጠረው ሁኔታ ድርድሩን አጓቶታል ያሉት ቃል አቀባዩ፥ ግድቡ ከተገደበ በኋላ የሃይል ማመንጨት ሂደቱን ሊያደናቅፍ የሚችል ምንም አይነት ሁኔታ ሊኖር አይችልም ብለዋል።
ከናይል ወንዝ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ በኩል ምንም አይነት የአቋም ለውጥ እንደሌለ ተመልክቷል።
ኢትዮጵያ የምታመነጨው ሃይል ሱዳንን እና ግብጽንም ተጠቃሚ እንደሚያደርግ በመጥቀስ በጅቡቲ የተጀመረው የሃይል አቅርቦት በቀጣይ ወደ ኬንያ እና ወደ ሌሎች አካባቢዎች እየተስፋፋ እንደሚሄድ ተናግረዋል
በወንደወሰን አረጋኸኝ