Fana: At a Speed of Life!

በማኅበር ለመደራጀት የተመዘገቡ የ20/80 እና የ40/60 ቤት ፈላጊዎችን ወደተግባር ለማስገባት ቅድመ ዝግጅት ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 17፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኅብረት ሥራ ማኅበር ለመደራጀት የተመዘገቡ የ20/80 እና የ40/60 ቤት ፈላጊዎች ወደ ተግባር ለማስገባት ዝግጅት ማጠናቀቁን የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ አስታውቋል፡፡

ቢሮው ፍላጎት ያላቸውን ነባር የ20/80 እና የ40/60 የማኅበር ቤት ፈላጊዎችን በኅብረት ሥራ ማኅበር ተደራጅተው እንዲሰሩ በኦንላይን ምዝገባ ማካሄዱ የሚታወስ ነው፡፡

ካሉት አማራጭ የቤት አቅርቦት ውስጥ አንዱ የሆነውን የማኅበር ቤት ተግባራዊ ለማድረግ የዲዛይን ዝግጅት ፣ የመሬት ዝግጅት እና የአበዳሪ ባንኮችን የመለየት ቅድመ ሁኔታዎችን በማጠናቀቅ ማኅበራቱ ተደራጅተው ወደ ተግባር የሚገቡበትን ሁኔታ ማመቻቸቱን ቢሮው አስታውቋል፡፡

በኦንላይን የተመዘገቡ የ20/80 እና የ40 /60 ቤት ፈላጊዎች አስፈላጊውን መረጃ እንዲያሟሉም ጠይቋል፡፡

ከዚህ በፊት በኦንላይን የተመዘገቡ የማኅበር ቤቱ ፈላጊዎች ሁሉ በመዲናዋ በራስም ሆነ በትዳር አጋር ስም ቤት ወይም ቤት መስሪያ ቦታ የሌላቸው ወይም ኖሯቸው ከ1997 ዓ.ም ወዲህ በስጦታ ወይም በሽያጭ ያላስተላለፉ መሆኑን የሚያሳይ ማስረጃ” የሚገልፅ ቅፅ ከሚኖሩበት ወረዳ ቤቶች አስተዳደር ጽ/ቤት በመውሰድ ከየካቲት 16 እስከ መጋቢት 16 / 2014 ዓ.ም ድረስ በኦንላይን የተደረገውን ምዝገባ በአካል እንዲያረጋግጡ ቢሮው አስታውቋል።

ሁሉም ተመዝጋቢም በተጠቀሰው የጊዜ ገደብ ውስጥ ማስረጃውን ማቅረብ እንደሚጠበቅበትና ጊዜውን አሳልፈው ለሚመጡ ኃላፊነት እንደማይወስድ ማሳሰቡን ከከተማው ኮሙኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.