Fana: At a Speed of Life!

የካማሺ ሠላም እንዲመለስ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ቢሮው አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 17፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ካማሺ ዞን ሠላም በዘላቂነት እንዲረጋገጥ አስተዳደሩን በአዲስ መልክ ከማዋቀር ጀምሮ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን የክልሉ ሠላም ግንባታ እና ጸጥታ ቢሮ አስታወቀ፡፡

የክልሉ ሠላም ግንባታና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ሙሳ ሃሚድ ÷ አሸባሪው የህወሃት ቡድን የጥፋት ተላላኪዎቹን በማቀናጀት በዞኑ ከ2011 ጀምሮ ሠላም የማደፍረስ ሥራ ሲሰሩ እንደነበረ ገልጸዋል፡፡

በአሸባሪው የህወሓት ቡድን የሽብር ተግባርም የንጹን ሰዎች ሕይወት እንዳለፈና በርካቶች ከአካባቢያቸው እንደተፈናቀሉ ብሎም ከፍተኛ ግምት ያለው ንብረት መውደሙን አስረድተዋል፡፡

የክልሉ መንግስት የካማሺን ሠላም ወደ ቀደመ ሁኔታው ለመመለስ በቅርቡ የዞኑን አስተዳደር እንደገና ከማዋቀር ጀምሮ የተሻለ አመራር ሊሰጡ በሚችሉ አመራሮች እስከመተካት የደረሰ እርምጃ መውሰዳቸውንም አስታወቀዋል፤ ተከታታይ ጠንካራ ግምገማዎች እየተካሄዱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዞኑ የጸጥታ ችግር እንዲፈጠር ተሳትፎ የነበራቸው ግለሰቦች ተለይተው በፍርድ ቤት ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን አቶ ሙሳ ጠቅሰው፥ ጉዳያቸው በፍርድ ሂደት ላይ የሚገኙ እንዳሉም አመልክተዋል፡፡

በዞኑ እስከ ቀበሌ በመውረድ የሀገር ሽማግሌዎችን፣ ታዋቂ ሰዎች እና የሃይማት አባቶችን ያካተቱ ህዝባዊ የውይይቶች እና ችግሮችን በመለየት ለመፍታት መድረኮች መፈጠራቸውም ተጠቁሟል፡፡

ለተፈናቃዮች የሰብዓዊ ድጋፍ የማድረስ እና መልሶ የማቋቋም ፣ ለነዋሪው ደግሞ ሸቀጣ ሸቀጦች እንዲደርሱ ጥረት እየተደረገ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

በአሁኑ ወቅት ዞኑ በሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ በክልሉ ልዩ ሃይል ጠንካራ ጥበቃና የዞኑን ሚሊሻ በማሠልጠን ጸጥታ የማረጋገጥ ሥራ እየተሰራ ነው ተብሏል፡፡

በተጨማሪም ከኦሮሚያ ክልል ጋር በመቀናጀት የዞኑን ሠላም የማረጋገጥ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ምክትል ሃላፊው ገልጸዋል፡፡

በዞኑ ጉዳት የደረሰባቸውን ትምህርት ቤቶች በመጠገን ትምህርት እንደገና ለማስጀመር የተደረገውን ጥረት ለማጠናከር ጥረቶች መኖራቸውንም ተናግረዋል፡፡

አቶ ብጅጋ በበኩላቸው ካማሺ ዞን ወደ መረጋጋት እየመጣ መሆኑን ጠቅሰው ፥ ሠላም በዘላቂነት ለማረጋገጥ መንግስት ብቻ ሳይሆን ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሊረባረቡ ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.