ሽብርተኛው የሸኔ ቡድን በህዝብ ላይ እያደረሰ ያለውን ችግር ለማስወገድ እየተሰራ ነው -የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን
አዲስ አበባ፣ የካቲት 17፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው ሸኔ በህዝብ ላይ እያደረሰ ያለውን ችግር ለማስወገድ እየሰራ መሆኑን የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር እና የወንጀል ምርመራና ፍትህ ማሰጠት ዘርፍ ኃላፊ ግርማ ገላን እንደገለጹት÷ የጸጥታ ኃይሉ እና የመንግሥት አካላት አሸባሪው ሸኔ በንፁሃን ዜጎች ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ለማድረግ እና ለማስወገድ ከፍተኛ ዋጋ እየከፈለ ነው፡፡
የሸኔ ቡድን በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች የንፁሃን ዜጎችን ሕይወት ሲቀጥፍ፣ ንብረታቸውን ሲያወድምና ሲዘርፍ ከመቆየቱም በላይ፥ በመንግስት ተቋማት እና በተለያዩ መሰረተ ልማቶች ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በግጭቱ የሽብር ቡድኑ መሪዎች ንጹሃንን ከፊት እያሰለፉ ራሳቸው ከኋላ መሰለፋቸው ቡድኑን ለማጥፋት የተደረገው ሙከራ እስካሁን የተጠበቀውን ያህል ውጤታማ እንዳይሆን አድርጎታልም ነው ያሉት፡፡
የዜጎቻችን ሞትና ስቃይ በዚህ መልኩ መቀጠል የለበትም ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ÷ አስፈላጊውን ሁሉ ዋጋ ለመክፈል የጸጥታ ኃይሉ ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።
ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታትም ሁኔታውን መሬት ላይ ያለውን ሀቅ ባገናዘበ መልኩ ማጥናትና ቀጣይ አቅጣጫዎችንም በሰከነ መንገድ ማስቀመጥና መስራት እንደሚገባ ነው ምክትል ኮሚሽነሩ የተናገሩት፡፡
የፖለቲካ አመራሩ እና በጸጥታ ኃይሉ እስካሁን ሲያደርጉት የነበረውን ጥረት በማጠናከር ችግሩን በሚመጥን መልኩ በጋራ መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።
ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ በሚደረገው እንቅስቃሴም ህብረተሰቡ እንደተለመደው ከመንግስት እና ከጸጥታ ኃይሉ ጎን እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በአፈወርቅ አለሙ
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!