በተለያዩ ቦታዎች የተፈጸሙ ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለማጣራት ለተቋቋመው የምርመራ ቡድን ስልጠና እየተሰጠ ነው
አዲስ አበባ፣ የካቲት 17፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ) በትግራይ፣ አፋር እና አማራ ክልሎች የተፈጸሙ ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለማጣራት ለተቋቋመው የምርመራ ቡድን አለም አቀፋዊ ደረጃውን የጠበቀ የወንጀል ምርመራ ለማካሄድ የሚያስችል ስልጠና በአዳማ ከተማ እየተሰጠ ነው፡፡
ስልጠናው በተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽን፣ የተባበሩት መንግስታት የአደገኛ መድሀኒትና እና ወንጀል መከላከል ጽህፈት ቤት እንዲሁም በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ትብብር የተዘጋጀ እና በልዩ የወንጀል ምርመራ አካሄድ ላይ ያተኮረ መሆኑ ተገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እና የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ፅህፈት ቤት ጥምር ቡድን በትግራይ ክልል የተፈፀሙ የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በማጣራት ጥቅምት 2014 ዓ.ም ዝርዝር ግኝቱን ይፋ ማድረጉም ተመላክቷል፡፡
በጥምር ቡድኑ ሪፖርት ላይ የኢትዮጵያ መንግስት ሀይሎችን ጨምሮ በግጭቱ ተሳትፎ የነበራቸው አካላት ሁሉ በተለያየ ደረጃ የሚገለፅ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መፈፀማቸውም ተገልጿል።
የኢትዮጵያ መንግስት በሪፖርቱ ላይ የተመለከቱ ማጠቃለያዎች እና ግኝቶችን የሚቀበል መሆኑን፣ ምክረ-ሃሳቦቹን ወደተጨባጭ የፍትህ ስራ ለመመለስም ተፈፀሙ የተባሉትን ከባድ የወንጀል ድርጊቶች ሁሉ – የፍትህ ስርዓቱን በመጠቀም እና በማጣራት የወንጀል እና የአስተዳደር ተጠያቂነትን እንደሚያሰፍን ቃል ግብቷልም ነው የተባለው፡፡
የዚህ ዝግጅት አንድ ክፍል የሆነውና በጥምር ቡድኑ የምርመራ ሪፖርት ላይ የተመለከተው ዋና ምክረ-ሀሳብ መንግስት የሚያካሂደው የከባድ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ምርመራ ሁሉን አቀፍ፣ ነጻ እና አለማቀፋዊ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ እንዲካሄድ ማድረግ መሆኑም ተገልጿል።
በዚህ መሰረት መንግስት ከፌዴራል አቃቤ ህግ፣ ከፌዴራል ፖሊስ እና ከክልል ፍትህ ቢሮዎች የተውጣጡ አባላትን የያዘ አስር ከፍተኛ የወንጀል ምርመራ ቡድኖችን አደራጅቷልም ነው የተባለው።
ይህ ስልጠና በሶስቱም ተቋማት እና ለዚሁ አላማ በተቋቋመው የሚኒስትሮች ግብረ-ሀይል ሴክሬታሪያት ትብብር የተዘጋጀ መሆኑም ተመላክቷል።
በግጭቱ ተሳታፊ ተዋናዮች የተፈፀሙ ጥፋቶች ምርመራን በማካሄድ ግልፅ እና ከተፅእኖ ነፃ በሆነ ሂደት ምርመራ በማድረግ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ እንዲችሉ ያደርጋልም ነው የተባለው፡፡
በአለም አቀፍ ደረጃ የተሻሉ ተመክሮዎች አሰራር ላይ የተመረኮዘ ምርመራን በማካሄድ የወንጀል እና የአስተዳደር ተጠያቂነትን በተጨባጭ ለማረጋገጥ ያለውን የፖለቲካ ቁርጠኝነት በግልፅ የሚያሳይ እንደሚሆን ከፍትህ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!