Fana: At a Speed of Life!

አሸባሪውን የህወሓት ቡድን ከወንጀል ተጠያቂነት ነጻ ማድረግ ግጭቱን በሠላም ለመፍታት አያስችልም – አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን

አዲስ አበባ፣ የካቲት 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪውን የህወሓት ቡድን ከወንጀል ተጠያቂነት ነጻ ማድረግ ግጭቱን በሠላማዊ መንገድ ለመፍታት አያስችልም ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ገለጹ፡፡

አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በኖርዌይ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ሄንሪክ ቱን የተመራውን ልዑክ በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡

በሀገራቱ የሁለትዮሽ ግንኙነት እና በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ያተኮረ ውይይት ማድረጋቸውንም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

አምባሳደር ሬድዋን በኢትዮጵያ እና ኖርዌይ መካከል ለረጅም ጊዜ የዘለቀውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እና ትብብር አድንቀው፥ ኖርዌይ ኢትዮጵያ እየተገበረች ላለችው አረንጓዴ ኢኮኖሚ እና የተሃድሶ አጀንዳዎች ድጋፏን በማሳየቷ አመስግነዋል፡፡

ኖርዌይ፥ ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል የሕግ ማስከበር እርምጃዎችን እየወሰደች ባለችበት ወቅት ሰብዓዊ መብት እንዳይጣስ ስታሳስብ እንደነበረና ሰብዓዊ አቅርቦት ወደ ሰሜኑ የሀገራችን ክፍል እንዲደርስ ድምጽ ስታሰማ እንደነበረም አስታውሰዋል፡፡

አምባሳደር ሬድዋን፥ የህወሓት ቡድንን ተፈጥሯዊ ባህሪ እና ግጭቱ የተካሄደበት ተጨባጭ ሁኔታ በመገንዘብ የተደረገ እንቅስቃሴ ቢኖር ኖሮ ግጭቱን በአጭር ጊዜ መቋጨት ይቻል ነበር ብለዋል።

አክለውም ጸብ አጫሪ ባህሪ የተጠናወተው የህወሓት ቡድን ባለው የስግብግብነት እና የበላይ የመሆን አባዜ ተነሳስቶ በሰሜን እዝ ላይ ባደረሰው ጥቃት ግጭቱ መጀመሩን አንስተው፥ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ግን ይህን እውነታ ወደ ጎን በመተው ህወሓትን ተጠቂ አድርጎ ለመሳል ረጅም ርቀት መጓዙን ገልጸዋል።

መንግሥትም በሀገሪቱ ዘላቂ ሠላም እንዲሰፍን ባለው ጽኑ ፍላጎት አወንታዊ እርምጃዎች መውሰዱን ሚኒስትር ዴኤታው አንስተዋል፡፡

መንግሥት እስረኞችን መፍታቱ እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማንሳቱም ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ ምክክር ለማካሄድ ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነውም ብለዋል፡፡

መንግሥት ለሠላም ካለው ቁርጠኝነት የተነሳም ሠራዊቱ ወደ ትግራይ ክልል እንዳይገባ ማድረጉን እንዲሁም የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት እንዲሳለጥ የተቻለውን ጥረት ሁሉ ማድርጉን ተናግረዋል፡፡

ምንም እንኳ በመንግስት በኩል የተለያዩ አወንታዊ እርምጃዎች እየተወሰዱ ቢሆንም፥ የህወሓት የሽብር ቡድን ግን በአፋር በኩል አዲስ ጥቃት በመክፈት የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት እንዲስተጓጎል ማድረጉን አስረድተዋል፡፡

አያይዘውም ግጭቱ እንዲቆም ከተፈለገ የቡድኑን ጸብ አጫሪነትና የሚፈጽማቸውን የግፍ ተግባራት በማያወላዳ ሁኔታ መኮነን እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.