Fana: At a Speed of Life!

በሀረር ከተማ የተገነባው የካንሰር ህክምና ማዕከል አገልግሎት መስጠት ጀመረ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሀረር ከተማ በሚገኘው ሐረማያ ዩኒቨርስቲ ህይወት ፋና አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ውስጥ የተገነባው የካንሠር ህክምና መስጫ ማዕከል ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ ።

የሐረማያ ዩኒቨርስቲ ለህንፃ ግንባታው ከ65 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ያደረገበት ሲሆን፥ ለማዕከሉ የሚያስፈልጉ የጨረር ህክምና መስጫ መሳሪያዎችን ደግሞ የጤና ሚኒስቴር ከአጋሮቹ ጋር በመተባበር ከ4 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ ወጪ በማድረግ አሟልቷል።

የህክምና ማዕከሉ የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ በተገኙበት ተመርቆ ወደ ስራ መግባቱ ተገልጿል፡፡

ሚኒስትሯ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ በኢትዮጵያ ለመገንባት በታቀዱት ሰባት የካንሠር ህክምና መስጫ ማዕከላት መካከል ከአዲሰ አበባ ጥቁር አንበሳ እና በጅማ ሆስፒታሎች በመቀጠል 3ኛው የካንሰር ህክምና ማእከል ይሆናል፡፡

የማዕከላቱ መገንባትና ወደ ስራ መግባት ታማሚዎች በመኖሪያ አካባቢያቸው ህክምናን እንዲያገኙ በማድረግ ህመሙ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ ጉልህ ሚና እንዳለው ሚኒስትሯ ጠቁመው የጤና ሚኒስቴር ካንሠርን ጨምሮ ሌሎች ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

የሀረሪ ክልል ምክትል ርዕስ መስተዳድር ወ/ሮ ሚስራ አብደላ በበኩላቸው የማዕከሉ በሀረር ከተማ መገንባት ለምስራቅ ኢትዮጵያ ህዝብ በሚሰጠው ጠቀሜታ ባለፈ የሐረሪ ክልልን የጤና ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ ለተጀመረው እንቅስቃሴ አጋዥ ይሆናል ብለዋል።

ተመርቆ ስራ የጀመረው የካንሠር የጨረር ህክምና መስጫ ማዕከል በየቀኑ 60 ለሚሆኑ ታማሚዎች የህክምና አገልግሎት ይሰጣል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተገልጿል፡፡

በተሾመ ኃይሉ

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.