“ድርቅ በተፈጥሮ ቢመጣም ርሃብ የስንፍናችን ውጤት ነው” – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) “ድርቅ በተፈጥሮ ቢመጣም ርሃብ የስንፍናችን ውጤት ነው” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፥ “ለድርቅና ርሃብ ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት እየተረባረብን፣ አፋጣኝ ምላሽ ለሚሹ ወገኖቻችንም አቅማችን የፈቀደውን እናድርግ” ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ያስተላለፉት መልዕክት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፦
“ድርቅ በተፈጥሮ ቢመጣም ርሃብ ግን የሥንፍናችን ውጤት ነው!”
በየአሥር ዓመቱ እየተመላለሰ እንደሚጎበኘን ድርቅና ርሃብ ልክ በታሪካችን የፈተነን ጠላት የለም። አያሌ ውድ ዜጎቻችንን ሕይወት ቀጥፏል። በምግብ ራሳችንን ያለመቻል ችግር ህጻናትን ለመቀንጨር፣ ወጣቶችን ለስደት፣ አረጋውያንን ለጉስቁልና፣ የቀንድና ጋማ ከብቶቻችንን ለእልቂት ዳርጓል። ቅኝ ሊገዙን የመጡ የውጭ ወራሪዎች በርሃብና ቸነፈር ልክ አልፈተኑንም። ዳር ድንበራችን እንዳይነካ፣ ሉአላዊነታችን እንዳይደፈር የምናድርጋቸው ተጋድሎዎች በርሃብና ቸነፈር ላይ አለመደገማቸውን ያህል ዋጋ እንዳስከፈሉን አስረጅ አያሻውም። ርሃብ የሀገራችን ምስል ላይ ጥቁር ነጥብ አስቀምጦአል።
በምግብ ራሳችንን ባለመቻላችን ምክንያት ብሄራዊ ህልውናችን ጥላ አጥልቶበት መታየቱ ሊቆጨን ይገባል። የእለት ጉርሳችንን አሸንፈን እስካልተገኘን ድረስ በየትኛውም ዘርፍ የምናስመዘግበው ስኬት ትርጉሙ ይደበዝዛል። በግብርና ምርቶች ላይ የምናሳየው ድክመት በኢኮኖሚው ብቻ ሳይሆን በማህበራዊም፣ በፖለቲካውም፣ በዲፕሎማሲና በሌሎች ዘርፎችም ላይ ተጽእኖ አለው። ለግብርና ተስማሚ ለም መሬትና ወንዞች ኖረውን የእርዳታ በሮችን የምናንኳኳው፣ ታሪክ ኖሮን ጎልተን የማንታየው፣ እምቅ የዲፕሎማሲ አቅም እያለን በዓለም መድረኮች የማንደመጠው – በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ – ጊዜ እየጠበቀ በሚጎበኘን ድርቅ እና ርሃብ ምክንያት ነው።
ተደጋግሞ እንደሚባለውም ድርቅ በተፈጥሮ ቢመጣም ርሃብ ግን ሰው ሠራሽ ነው፤ ሥንፍናችንና ደካማ የግብርና ፖሊሲዎቻችን የፈጠሩት ችግር ነው። በምግብ ራስን የመቻል ጉዳይ፣ በዘላቂነት ከርሃብና ቸነፈር የመላቀቅ ጉዞ ለጥቂቶች የሚተው፣ ወይም ለጥቂት ጊዜ የሚቀነቀን አጀንዳ አይደለም፤ እንደ ሀገር ተባብረን ልናሸንፈው የሚገባ የጋራ ጉዳያችን ነው። ገልጠን፣ መርምረንና ለፍተንበት የምንለውጠው እንጂ ሸፋፍነንና ደብቀን ፈጽሞ ሊንሻገረው አንችልም። ያለን ምርጫ አንድነው፤ ተረባርበን ዘላቂ መፍትሄ መስጠት።
ባንኮች ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ የቆጠበውን ገንዘብ ተጠቅማችሁ የአገልግሎትና የግንባታው ዘርፍን ፋይናንስ በማድረግ በዚያ በኩል ለውጥ እንዳመጣችሁ ሁሉ፥ ግብርናውንም ፋይናንስ በማድረግ የምትክሱበትን መንገድ መቀየስ አለባችሁ። ከምርጥ ዘርና የግብርና ግብዓትና መሳሪያዎች አቅርቦት ጋር በተገናኘ መሥራት ለሚፈልጉ አካላት ልዩ ልዩ ማበረታቻዎችን መንግሥት ያዘጋጃል። በኩታ ገጠም የሚያርሱ አርሶ አደሮችም ሆኑ፥ በሠፋፊ የመስኖ ግብርና ላይ የሚሠማሩ የግል ኢንቨስተሮች በተለያዩ መንገዶች ይበረታታሉ።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ፣ በአሁኑ ሰዓት በድርቅ ምክንያት እየተሰቃዩ የሚገኙ የሶማሌና የቦረና አርብቶ አደር ወገኖቻችን አፋጣኝ እርዳታችንን ይሻሉ። በመኖና የውሃ እጦት ከብቶቻቸው እየረገፉ ነው። ድርቁ ያስከተለው ርሃብ የሕጻናቱንና የአረጋውያኑን ሕይወት እያሳጣ ነው። ክረምቱ እስኪደርስላቸው እንጠብቅ ከተባለ ብዙ ወገኖቻችንን እናጣለን። ለድርቅና ርሃብ ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት እየተረባረብን፣ አፋጣኝ ምላሽ ለሚሹ ወገኖቻችንም አቅማችን የፈቀደውን እንድናደርግ በዚሁ አጋጣሚ ጥሪዬን አቀርባለሁ።
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!
ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!
የካቲት 18፣ 2014 ዓ.ም